AMN – የካቲት 14/2018 ዓ.ም
በ27ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ማንችስተር ሲቲ አርሰናል የሰጠውን ወርቃማ ዕድል ለመጠቀም ኒውካስትል ዩናይትድን ያስተናግዳል።
ማንችስተር ሲቲ ዛሬ ካሸነፈ በሁለት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎቹ ነጥብ ከጣለው መሪው አርሰናል በሁለት ነጥብ ብቻ ይርቃል።
የፔፕ ጋርዲዮላው ቡድን ምንም እንኳን በግርምት አፍ የሚያስዝ አቋም ላይ ባይገኝም የአርሰናል ነጥብ መጣል ተስፋ ሰጥቶታል።
ዛሬ ምሽት 5 ሰዓት በኢትሃድ ኒውካስትል ዩናይትድን ሲያስተናግድ ሙሉ ሦስት ነጥቡን ለመውሰድ ይፋለማል ተብሎ ይጠበቃል።
በሳምንቱ አጋማሽ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጦ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ጥሎ ማለፍ የመጀመሪያ ጨዋታ የአዘርባጂያውን ካራባግ 6ለ1 ያሸነፈው ኒውካስትል ከሲቲ ጋር ያለው ክብረወሰን ጥሩ አይደለም።
በተለይ በኢትሃድ ያስመዘገባቸው ቁጥሮች አንገት የሚያስደፉ ናቸው።
የኤዲ ሀው ቡድን ወደ ኢትሃድ ተጉዞ ባደረጋቸው 21 የመጨረሻ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች አንዱንም ማሸነፍ አልቻለም። በ16ቱ ሲረታ ፤ በአምስቱ ነጥብ ተጋርቷል።
ኒውካስትል ላይ ያለውን የበላይነት ለማስቀጠል የተዘጋጀው ማንችስተር ሲቲ በዛሬው ጨዋታ ወሳኝ አጥቂው ኧርሊንግ ሃላንድን መልሶ ያገኛል። ኖርዌያዊው አጥቂ ፉልሃምን 3ለ0 ባሸነፉበት ጨዋታ መጠነኛ የጉልበት ጉዳት ገጥሞት ተቀይሮ ወጥቶ ነበር።
ኒውካስትል ዩናይትድ አምበሉ ቡርኖ ጉማይሬሽን ማሰለፍ አይችልም። ብራዚላዊው አማካይ እስከ አራት ሳምንታት የሚያርቅ የጡንቻ ጉዳት ገጥሞታል።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ ቼልሲ ከበርንሌይ ፣ አስቶንቪላ ከሊድስ ዩናይትድ እንዲሁም ብሬንትፎርድ ከብራይተን ይጫወታሉ። ምሽት 2:30 ዌስትሃም ዩናይትድ ከቦርንማውዝ የሚያደርጉትም ጨዋታ የዛሬ መርሐግብር አካል ነው።
በሸዋንግዛው ግርማ