ዘመናትን የተሻገረ ወዳጅነት

You are currently viewing ዘመናትን የተሻገረ ወዳጅነት

ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋት ያላት አስፈላጊነት ይበልጥ እያደገ መምጣቱ ተመላክቷል                           

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ታሪክ እንደ ራስ ዳሸን ከፍ ያለ ነው፤ እንደ ጣናም የሰፋ፤ እንደ ዳሎልም የጠለቀ፤ እንደ ዓባይም የገዘፈ፤ እንደ ንጋት ሐይቅም በድል የተንጣለለ ነው፡፡ በእርግጥም ጥንታዊው የዲፕሎማሲ መዝገብ ሲገለጥ ከዓድዋ ድል ንግስቷ እና ከቀይ ባሕሯ እመቤት ኢትዮጵያ ጋር ለመወዳጀት በርካቶች አድማስ ጥሰው ባሕር አቋርጠው መጥተዋል፡፡ በዚህ እውነት ውስጥም ቱርክዬ አለች፡፡

የሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት የጀመረው በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኦቶማን ኢምፓየር የቀይ ባሕር ወደቦችን ሲቆጣጠር መሆኑን ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉት የታሪክ ባለሙያው ጀማል ሽፈራው (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡

እንደ ታሪክ ባለሙያው ገለፃ ዘመን ተሻጋሪው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በሂደት ወደ ዘላቂ እና ተግባራዊ ዲፕሎማሲያዊ ትስስር ከፍ ብሏል፡፡ ይህንንም ተከትሎ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1896 ሱልጣን አብዱልሀሚድ 2ኛ እና ዳግማዊ አጼ ሚኒሊክ ይፋዊ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመጀመራቸው ቱርክዬ በ1912 በሐረር ቆንስላ ጽህፈት ቤቷን ከፈተች፡፡ በመቀጠልም እ.ኤ.አ በ1926 ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ ቀለሰች፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ በ1933 ኤምባሲዋን በአንካራ መክፈት ቻለች፡፡

የ19ኛው ክፍለ ዘመን ዲፕሎማሲያዊ ልውውጦች በሀገራቱ ጠንካራ የኢኮኖሚ አጋርነት እንዲገነባ፣ ኢንቨስትመንት እና መሠረተ ልማት እንዲስፋፋ፣ ንግድ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲያድግ ማድረጉንም የታሪክ ባለሙያው ጀማል (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡

ዘመናትን ያስቆጠረው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በታሪክ ላይ የተመሰረተ፣ በኢኮኖሚ የተጠናከረ እና በስትራቴጂካዊ ትብብር ከፍታውን አስጠብቆ የቀጠለ ነው፡፡ ለዚህም የሰሞኑ የቱርክዬ ፕሬዝዳንት ረጅብ ጣይፕ ኤርዶዋን የኢትዮጵያ ጉብኝት እና በተለያዩ ጊዜያት በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረጉ የተለያዩ ስምምነቶች ማሳያ መሆናቸውን የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አቶ አህመድ ሰይድ ይናገራሉ፡፡

በሀገራቱ መካከል ያለው የልማት ትብብር እና የሰብዓዊ ተሳትፎ ከፍ ያለ መሆኑን የሚገልፁት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ገነነ ካሳዬ ለአብነትም የሆስፒታል ግንባታ፣ የህክምና መሳሪያዎች ድጋፍ፣ የሙያ ስልጠና፣ ሰብዓዊ እርዳታ፣ የምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች፣ የስደተኞች ድጋፍ፣ የውሃ አቅርቦት ፕሮጀክቶች እና በተለይም በከተሞች የማዘጋጃ ቤት አቅም ግንባታ ላይ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገች እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አቶ አህመድ ሰይድ እንደሚሉት ደግሞ ከምጣኔ ሀብት ባሻገር ሀገሪቱ በሰላምና በደህንነት ዙሪያ በአፍሪካ ቀንድ ያላት እንቅስቃሴም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

በተለይም የአፍሪካ ቀንድ በዓለም ላይ በጣም ሚስጥራዊ ከሆኑ የባሕር መስመሮች መካከል አንዱ በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ ኮሪደር አቅራቢያ ይገኛል። በመሆኑም በዚህ ክልል ውስጥ ያለው መረጋጋት በዓለም አቀፍ ንግድ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ከፍ ያለ ነው። ይህንን እውነት በውል የተረዳችው ቱርክዬ ደግሞ በቀጣናው ሁለንተናዊ አቅም ካላት ኢትዮጵያ ጋር በየጊዜው የተለያዩ ወሳኝ ስምምነቶችን  እያደረገች መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ገነነ እንደሚሉት የትራንስፖርት ትስስር በግንኙነቱ ውስጥ ስትራቴጂካዊ ሚና ይጫወታል። ለዚህ ደግሞ ገናና ስም ያላቸው ሁለቱ አየር መንገዶች ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡ በመሆኑም በአዲስ አበባ እና በኢስታንቡል መካከል የሚደረጉ በረራዎች ምስራቅ አፍሪካን በቀጥታ ከአውሮፓ እና ከእስያ ጋር በዋና ዋና የአየር መንገድ ማዕከላት ያገናኛሉ። ይህም ቱሪዝምን በማስፋፋትና ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎችን ለማጎልበት የሚኖረው ድርሻ ከፍ ያለ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ እና ቱርክዬ ግንኙነት ወደ ሶስት ታላላቅና ተስፋ ሰጭ ደረጃዎች እየተሸጋገረ መሆኑን የሚናገሩት የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው ይሄውም ስኬታማ የሆነ የንግድ ሽርክና (የእቃ እና የኢንቨስትመንት ልውውጥ።)፣ እያደገ ያለ የኢንዱስትሪ ሽርክና (የጋራ ምርት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር) እንዲሁም ኢትዮጵያን የበለጠ የአፍሪካ የገበያ የማምረቻ ማዕከል ሊያደርግ የሚችል የምርት ጥምረት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ከፍታ የሚያመላክቱ ናቸውም ብለዋል፡፡

ባሳለፍነው ማክሰኞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ካደረጉት የቱርክዬ ፕሬዝዳንት ረጅብ ጣይፕ ኤርዶዋን ጋር የጋራ መግለጫ መስጠታቸው አይዘነጋም። በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እንዳሉት በመከባበር፣ በመደጋገፍና አብሮ በመስራት ከጥንት ጀምሮ የነበረውን የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት ለማጠናከር ከፕሬዝዳንቱ ጋር ከስምምነት መድረሳቸውን ገልፀዋል፡፡

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ ፕሬዝዳንት ረጅብ ጣይፕ ኤርዶዋን የቀጠናውን ሁኔታ የሚገነዘቡ በመሆናቸው በሁለትዮሽና የባለ ብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ ያደረጉት ውይይት እጅግ ፍሬያማ ነበር፡፡ ፕሬዝዳንቱ፣ ኢትዮጵያ በቀጣናው ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆኗንና  ሚናዋን  መወጣት እንዳለባት ያምናሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለዚህም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፖለቲካና ዲፕሎማሲ ተፅዕኖ ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፣ ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበች የምትገኘው አፍሪካ በሚቀጥሉት ዓመታትም የሚገባትን ቦታ እንድትይዝ እየተሠራ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን በበኩላቸው ኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ የመጀመሪያው የእስልምና መዳረሻ እና የፍትሐዊው ንጉሥ ነጃሺ መገኛ መሆኗ ለሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጠናከር ትልቅ መሠረት መሆኑን ገልጸዋል። ይህ ጥንታዊ እና ታሪካዊ ወዳጅነት ዛሬም በልማት እና በዲፕሎማሲያዊ ትብብር ደምቆ መቀጠሉን አክለዋል።

የቱርክዬ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (TIKA) ታሪካዊውን የንጉሥ ነጃሺ መስጂድ እና የንጉሡን መካነ መቃብር ዕድሳት ማጠናቀቁን ጠቅሰው፣ ይህም የሁለቱን ሀገራት እና ሕዝቦች ታሪካዊ ትስስር ይበልጥ እንደሚያጠናክረው መስክረዋል፡፡

የቱርክዬ ማሪፍ ፋውንዴሽንም በሀገራቸው እና በኢትዮጵያ መካከል የትምህርትና የባህል ድልድይ በመሆን የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ይበልጥ የማቀራረብ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን አረጋግጠዋል።

ፕሬዝዳንቱ  አክለውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መስኮች ላስመዘገቡት ስኬት “እንኳን ደስ አለዎት” በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል። ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን ረጅም የሀገረ መንግሥት ታሪክ እና የተረጋጋ አስተዳደር ያላት ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋት አስፈላጊነቷ ይበልጥ እያደገ መምጣቱንም መስክረዋል፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በኢትዮጵያ ከ260 በላይ የቱርክዬ ኩባንያዎች ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት የኢንቨስትመንት ተሳትፎ የሚያደርጉ ሲሆን፣ በ10 ሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዋናነት ቡና እና ጥራጥሬዎችን ጨምሮ እንደ ሰሊጥና ተልባ ያሉ የቅባት እህሎችን ወደ ቱርክዬ የምትልክ ሲሆን፣ ለአብነትም በፈረንጆቹ 2024 ከ42 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ምርት ወደ ቱርክዬ ልካለች። በአንጻሩ ቱርክዬ ወደ ኢትዮጵያ ከምትልካቸው ምርቶች መካከል ለግንባታ ግብዓት የሚሆን ብረታ ብረት፣ መድኃኒትና የኢንዱስትሪ ግብዓቶች በዋናነት ይጠቀሳሉ።

የቱርክዬ ብሔራዊ ምክር ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ በ2013 በሀገራቱ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ መጠን 421 ሚሊዮን ዶላር ነበር፤ እ.ኤ.አ በ2020 ወደ 842 ሚሊዮን ዶላር አድጓል፡፡ የሀገራቱ መሪዎች ከሰሞኑ በአዲስ አበባ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ቢያንስ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ እና ከዚያም በላይ ለማሳደግ አቅደዋል፡፡

በነሐሴ 2021 የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቱርክ ፕሬዝዳንት ረጅብ ጣይፕ ኤርዶዋን ግብዣ መሰረት ወደ ቱርክዬ ኦፊሴላዊ ጉብኝት አድርገዋል። በዚህ ጉብኝት ወቅት፣ ሁለቱ ሀገራት በወታደራዊ ስልጠና እና ትምህርት ትብብር፣ በጋራ ልምምዶች መሳተፍ፣ በመከላከያ ኢንዱስትሪ፣ በወታደራዊ መረጃ ልውውጥ እና በሎጂስቲክስ ድጋፍ ላይ የተደነገገ ወታደራዊ ማዕቀፍ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡

ባሳለፍነው ማክሰኞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከፕሬዝዳንት ረጅብ ጣይፕ ኤርዶዋን ጋር በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በሰጡት የጋራ መግለጫ ሁለቱ ሀገራት በጋራ ለመፈፀም የተግባቡባቸውን የስምምነት አጀንዳዎች እና ነጥቦች ዘርዝረዋል። 

በዚህም የዘርፍ ብዝሃነት (Diversification)፣ የንግድ ግንኙነቱ በተወሰኑ ምርቶች ላይ ብቻ ሳይወሰን የተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎችን እንዲያካትት ስምምነት ላይ ተደርሷል። ታዋቂ የቱርክዬ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ ለሀገር ውስጥ እና ለጠቅላላው የአፍሪካ ገበያ የሚሆኑ ምርቶችን እንዲያመርቱ እና ኤክስፖርት እንዲያደርጉ ድጋፍ ለማድረግ ተስማምተዋል።

ኢትዮጵያ ያቀደችውን የ10 ነጥብ 2 በመቶ ዕቅድ ለማሳካት የባሕር በር ወሳኝ በመሆኑ በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር እንድታገኝ ቱርክዬ በዲፕሎማሲው መስክ የራሷን ጫና በመፍጠር የበኩሏን ሚና እንድትጫወት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውም ተገልጿል።

በሌላ በኩልም ኢትዮጵያ እና ቱርክዬ በፀረ-ሽብር ትግሉ ዙሪያ በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል። የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ ቱርክዬ ዘንድሮ የምታዘጋጀውን የኮፕ (COP) ስብሰባ በሚቀጥለው ዓመት ለኢትዮጵያ የምታስረክብ ሲሆን በዝግጅት ሂደት ውስጥ የልምድ ልውውጥ እና መደጋገፍ ለማድረግ ሀገራቱ ስምምነት ላይ ከደረሱባቸው ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

በቱርክዬ የመጀመሪያው የፕሬዝዳንት ጉብኝት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት የተካሄደው እ.ኤ.አ መጋቢት 1967 ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በቱርክ ካደረጉት ጉብኝት በመቀጠል በወቅቱ የቱርክ ፕሬዝዳንት የነበሩት ሴቭዴት ሱናይ እ.ኤ.አ ታህሳስ 1969 በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ መሆኑን ዋና መቀመጫውን በአንካራ ያደረገውና በቱርክዬ፣ በአውሮፓ፣ በአፍሪካ እና በምዕራብ እና ደቡባዊ እስያ ላይ ያተኮሩ ዓለም አቀፍ ዜናዎችን እና ወቅታዊ ጉዳዮችን በመዘገብ የሚታወቀው TRT World “How Turkey built ties with the African continent over 23 years” በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ መጋቢት 2021 ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review