የጋራ ትብብርን የሚሻው ሰላም

You are currently viewing የጋራ ትብብርን የሚሻው ሰላም
  • ህብረተሰቡ ሰላምን ለማስጠበቅ በተዘረጉ አደረጃጀቶች ያላቸው ተሳትፎ እንዲጠናከር የመገናኛ ብዙሃን ሚና ከፍተኛ መሆነ ተጠቁሟል

ያለንበት ዘመን መረጃ ከምንጊዜም በላይ ትልቅ አቅም የሆነበት ነው፡፡ ህብረተሰቡ በእለት ተለት ህይወቱ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ፣ ተሳትፎና ውሳኔ መረጃ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ በዚህ ረገድም መገናኛ ብዙሃን እውነተኛ፣ ወቅታዊና ትክክለኛ የመረጃ ምንጭ በመሆን፣ ህብረተሰቡን በማስተማርና በማንቃት አይተኬ ሚና አላቸው፡፡

በ2023 ዓ.ም ተመራጭ የሜትሮፖሊታን ሚዲያ የመሆን ርዕይ ሰንቆ እየተጋ ይገኛል፡፡  የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት መፍትሄ የሚያመላክቱ፣ እያዝናኑ የሚያስተምሩ ይዘቶችን በተለያዩ የሚዲያ አማራጮቹ ተደራሽ እያደረገ ይገኛል፡፡

 የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ማዕከል፣ የአፍሪካ መዲና እና በዓለም ሦስተኛዋ የዲፕሎማሲ ከተማ የሆነችውን አዲስ አበባ ከተማን ማዕከል አድርጎ የሚሠራ እንደመሆኑም፣ የከተማዋን ዕድገትና የነዋሪውን ፍላጎት የሚመጥን ተወዳዳሪና ተመራጭ ሚዲያ ለመሆን በለውጥ ምዕራፍ ውስጥ ከገባ ሰንበትበት ብሏል። በሚያቀርባቸው እንደ ዋርካ፣ አገልጋይ፣ በጠረጴዛ በመሳሰሉ አሳታፊ፣ ሞጋችና መረጃ ሰጪ ፕሮግራሞች የሕዝብ አገልጋይነቱ በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል፡፡ ይህንንም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት፣ የሕዝብ ምክር ቤት አባላት፣ የከተማዋ ነዋሪዎች እና ሌሎችም በተለያዩ ጊዜያት መስክረዋል፡፡

የትውልድ ድምፅ የሆነው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የኅብረተሰቡን ፍላጎት ለማርካትና ይበልጥ ተልዕኮውን ለመወጣት ከተለያዩ ተቋማት ጋር አብሮ ለመሥራት ስምምነቶችን በማድረግ ላይ ነው፡፡ ከትናንት በስቲያም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ጋር አብሮ ለመሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራርሟል፡፡

የስምምነት ፊርማው በተደረገበት ወቅት የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ እንደገለጹት፣ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ መዲና፣ በዓለም ሦስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከልና በርካታ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የሚኖሩባት ከተማ ናት፡፡ ከዚህ አኳያ ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ፣ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄዱ፣ የከተማዋን ሰላም አስተማማኝ እና ዘላቂ እንዲሆን ማድረግ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡

አስተማማኝና ዘላቂነት ያለው ሰላም ለማረጋገጥ ከፀጥታ አስከባሪዎች ባሻገር ነዋሪዎችን የሰላም ባለቤት ማድረግ እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ወይዘሮ ሊዲያ፣ በሰላምና ፀጥታ ሥራዎች ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ሰላምን ለማስጠበቅ በሚፈጠሩ አደረጃጀቶች ያላቸው ተሳትፎ እንዲጠናከር በማድረግ ረገድ የመገናኛ ብዙኃን ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 ቢሮው ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር ያደረገው ስምምነት ማኅበረሰቡ የወንጀል ሥጋቶችን፣ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርና መሰል ተግባራትን በመጠቆም እንዲሳተፍ እና እነዚህን ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች በመከላከል ለፀጥታ ኃይሉ አጋዥ የሚሆንበትን ሁኔታ ለመፍጠር ያስችላል፡፡ መንግሥትና ሕዝብ በጋራ ተባብረው እንዲሠሩ ለማድረግ ያግዛል፡፡ የኃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ በተለያዩ ጊዜያት የሚታዩ ኃይማኖትን ሽፋን ያደረጉ የአክራሪነትና ጽንፈኝነት እሳቤዎችን በመታገል ሂደት ማኅበረሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረውና የተዛቡ እሳቤዎችን ለመቀየር እንደሚያስችል ኃላፊዋ አብራርተዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ተቋሙ የተሰጡትን ተግባርና ኃላፊነቶች ነዋሪዎች ተገንዝበው መብትና ግዴታቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ከሚዲያው ጋር ተባብሮ መሥራታቸው አቅም እንደሚሆናቸው የተናገሩት ወይዘሮ ሊዲያ፣ በሁለቱ ተቋማት መካከል የተደረገው ስምምነት በመዲናዋ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ፣ የቅድመ ወንጀል መከላከል ሥራዎችን ለማቀላጠፍ፣ የኅብረተሰቡን የተባባሪነት ግንዛቤ ለመጨመር፣ በከተማዋ እየተከናወነ ያለውን የሀገርን ገጽታ የቀየረ ልማት ለማስቀጠል የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ በበኩላቸው፣ አዲስ አበባ ከተማ ከዕለት ወደ ዕለት በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያላት ተቀባይነት እየጨመረ ይገኛል፡፡ ይህ የሆነውም ስኬታማ የልማት ተግባራት ከመከናወናቸው እኩል አስተማማኝ ሰላም ማስፈን በመቻሉ እንደሆነ አብራርተዋል። ሚዲያው ራሱን በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ አቅም በማሳደግ፣ በየጊዜው አዳዲስ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ፣ የማኅበረሰቡ ልሳን በመሆን፣ በቀን ሃያ አራት ሰዓት፣ በሳምንት ሰባት ቀን፣ በአምስት የሀገር ውስጥ እና በሁለት ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች መረጃዎችን ለአድማጭ፣ ተመልካች እንዲሁም አንባቢያን እያደረሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

“የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የከተማዋን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ነው፡፡ እነዚህን ሥራዎች ኅብረተሰቡ እንዲያውቃቸው ማድረግ ያስፈልጋል” ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክም ወደ ማኅበረሰቡ በመውረድ፣ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣትና ለሚመለከተው የመንግሥት አካል በማቅረብ በመንግሥትና ሕዝብ መካከል ድልድይ በመሆን እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ሚዲያው በተለያዩ ቋንቋዎች መረጃዎችን ተደራሽ እያደረገ እንደሆነ ያነሱት አቶ ካሳሁን፣ በቀጣይም ከከተማዋ ዕድገት ጋር አብሮ ለመራመድና የማኅበረሰቡን ፍላጎት ለማርካት በቁርጠኝነት እየሠራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ባለፈው መስከረም ወር የሚዲያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና የማኔጅመንት አባላት ወንጀልን አስቀድሞ የመከላከል፣ ሰላምንና የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ተልዕኮን በመያዝ እየሠራ በሚገኘው የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በመገኘት በቴክኖሎጂ አጠቃቀምና በተለያዩ ጉዳዮች ያከናወናቸውን የሪፎርም ሥራዎችን መጎብኘታቸውና ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

በወቅቱም የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ሕዝብና መንግሥትን እንደ ድልድይ ሆኖ በማገናኘት እየሠራቸው ያሉ ሥራዎች ይበል የሚያሰኙ ናቸው ብለዋል፡፡ ወንጀልን ለመከላከል የሚደረጉ ጥረቶችና በከተማዋ ውስጥ የሚከናወኑ ሁሉን አቀፍ ልማቶች ላይ ሕዝቡ የተሟላ መረጃ እንዲኖረው ከማድረግ አንጻር የሚሠራውን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ በበኩላቸው፣ ሚዲያው የፌዴራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት፣ በቴክኖሎጂ በመታገዝ የከተማውን ሰላም እና ፀጥታን በማስከበርና የትራፊክ እንቅስቃሴን በማሳለጥ በኩል የሚሠራቸው ተግባራትን በመከታተል ለሕዝብ ተደራሽ በማድረግ እንደሚሰራ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በከተማ ደረጃ ከዚህ በፊት አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ እና የከተማዋ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ፣ ሥራና ክህሎት ቢሮ፣ ትምህርት ቢሮ፣ ትራንስፖርት ቢሮን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ከሚዲያው ጋር ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡ ሚዲያው በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ (AMN) እና ኤ ኤም ኤን ፕላስ የቴሌቪዥን ቻናሎች፣ በኤፍኤም 96.3 ሬዲዮ፣ በአዲስ ልሳን ጋዜጣ፣ በዲጂታል ሚዲያ አማራጮች በከተማዋ የሚካሄዱ የልማት እንቅስቃሴዎች፣ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ፣ የመልካም አስተዳደር እና ሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ መረጃ ሰጪ፣ አስተማሪና አዝናኝ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ እየሠራ ይገኛል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review