ለአፍሪካ ከተሞች የለውጥ ፋና ወጊውልማት

You are currently viewing ለአፍሪካ ከተሞች የለውጥ ፋና ወጊውልማት

የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ በአህጉሩ የነፃነትና አንድነት ታሪክ ትልቅ ስፍራ አላት። አፍሪካውያን በጋራ ጉዳያቸው ላይ ተሰባስበው የሚወያዩባትና የሚመካከሩባት መዲናቸው ናት፡፡ የአፍሪካ የፖለቲካ መዲና እየተባለችም ትጠራለች፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስሟንና ሚናዋን በሚመጥን ደረጃ በሁለተናዊ መልኩ ለውጥ እያሳየች ትገኛለች፡፡ የከተማዋን ገፅታ ከቀየሩ ስራዎች መካከል የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ይጠቀሳል። ልማቱ መዲናዋን ዘመናዊ፣ ውብና ለነዋሪዎችና ጎብኚዎች ተስማሚ እንድትሆን እያደረጋት ይገኛል፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት የመዲናዋ ወንዝና የወንዝ ዳርቻዎች አይደለም ለመኖር፣ ለማየትና በአካባቢያቸው ለማለፍ የሚጠየፏቸው፣ የሚሰነፍጥ ሽታና በሽታ ምንጭ የነበሩ፣ ተፈጥሯዊ ቀለማቸውን አጥተው እንደተቃጠለ ናፍጣ የጠቆሩና የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃና መጣያ ሆነው በከፍተኛ ደረጃ የተበከሉ ነበሩ፡፡

በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በአዲስ አበባ ከእንጦጦ ተራራዎች አንስቶ እስከ አቃቂ ወንዝ ድረስ 51 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የወንዝ ዳርቻ ልማት እየተከናወነ ይገኛል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቁ ከዚህ ቀደም ለዝግጅት ክፍላችን እንደጠቆሙት፣ የወንዝ ዳርቻ ልማቱ የአዲስ አበባን የጎርፍ ተጋላጭነትን በመቀነስ፣ የህዝብ መናፈሻ ፓርኮችን በማበራከት፣ የብስክሌትና የመሮጫ መንገዶችን በመፍጠር፣ የቱሪዝም መዳረሻ በማድረግ፣ የከተማዋን ዕይታ በመለወጥ፣ የህብረተሰቡን ደህንነት በማሻሻል፣ በልማቱ ላይም ሆነ ከልማቱ በኋላ በርካታ የሥራ ዕድል በመፍጠር ትልቅ አቅምን እየፈጠረ ነው፡፡

የወንዝ ዳርቻ ልማቱ ድልድዮች፣ ግድብ፣ አረንጓዴ ቦታዎች፣ የህፃናት መጫወቻዎች፣ የህዝብ መፀዳጃ ቤቶች፣ የመዝናኛ ማዕከላት፣ የውኃ ትራንስፖርት እና የንግድ ማዕከላት፣ የእግር ጉዞ ማድረጊያና የመሮጫ ትራኮች፣ የብስክሌት መስመሮች፣ ወንዞች እንዳይበከሉ የሚያደርጉ የፍሳሽ ማስወገጃ መሰረተ ልማቶችን አካትቶ በመሰራት ላይ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅትም የከተማዋ ወንዞች ለዓይን ማራኪ፣ ፅዱና አረንጓዴ ሆነዋል፡፡ ተፈጥሯዊ ቀለማቸውን መያዝ ጀምረዋል። ነዋሪዎች የእረፍት ጊዜያቸውን ለማሳለፍ የሚመርጧቸው ስፍራዎች መሆን ችለዋል፡፡ ወደ መዲናዋ የሚመጡ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ የከተሞች ከንቲባዎች፣ ባለሙያዎችና የተለያዩ ዜጎች የሚጎበኟቸው፣ ልምድና ተሞክሮ የሚወስዱባቸው ሆነዋል፡፡

default

ከሁለት ሳምንት በፊት የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ባደረገው ጥናት በከተሞች የፋይናንስ አስተዳደር አዲስ አበባ ከስድስት የአፍሪካ ከተሞች ቀዳሚ መሆኗን በቅርቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ በከተሞች የተሞክሮ ልውውጥ ላይ ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ ከመጡት  የአፍሪካ ዋና ከተሞች ከንቲባዎችና አስተዳዳሪዎች መካከል የኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ምክትል አስተዳደሪ ጀምስ ሙችሪ አንዱ ናቸው፡፡

ሙችሪ ከሌሎች የአፍሪካ ከንቲባዎች ጋር በመሆን የአዲስ አበባን የወንዝ ዳርቻ ልማት በጎበኙበት ወቅት በሰጡት አስተያየት፤ “ያየነው ልማት ናይሮቢን ጨምሮ ሌሎች ከተሞችን ንጽህና ውብ ለማድረግ ምን መስራት እንዳለብን ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡ በናይሮቢ የሚገኙ ወንዞች የተበከሉና በዙሪያቸው ቆሻሻ ስላለ ለእይታ ደስ አይሉም፡፡ የአዲስ አበባ ልማት ጥሩ እቅድና ሀብት በመመደብ ምን መስራት እንደሚቻል ጥሩ ማሳያ ነው” ሲሉ የወንዝ ዳርቻ ልማቱን አድንቀዋል፡፡ ለተገኘው ውጤትም የከተማ አስተዳደሩን እና የፌዴራል መንግስቱን አመራሮችን ያደነቁት ምክትል አስተዳዳሪው፣ ይህ ተሞክሮ ተወስዶ በናይሮቢ የወንዝ ዳርቻ ልማት እየተተገበረ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የአዲስ አበባን ተሞክሮ በመውሰድ በናይሮቢ የወንዝ ዳርቻ ልማት ያስጀመሩት ባለፈው ዓመት ነበር። ፕሮጀክቱ የከተማዋን ውበት፣ ፅዳት እና ለኑሮ ያላትን የምቹነት ደረጃ ከፍ የማድረግ፣ የትራንስፖርት መሰረተ ልማትን የማዘመን እና የነዋሪውን እንቅስቃሴ የማቀላጠፍ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ ለነዋሪዎቿ እና ለጎብኚዎች የምትመች የነቃች ከተማ እንድትሆን ለሚያግዘው ፕሮጀክት 50 ቢሊዮን የኬንያ ሽልንግ ተበጅቶለታል፡፡

ፕሬዝዳንት ሩቶ ፕሮጀክቱን ይፋ ባደረጉበት ወቅት፤ “በሚቀጥሉት 24 ወራት ውስጥ በናይሮቢ እጅግ ፅዱና የሚያማምሩ ወንዞችን እንመለከታለን። የወንዞች መልሶ የማልማት ሥራው 50 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት፣ የትራንስፖርት እና መሰል አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማቶችን ባካተተ መልኩ የሚተገበር ነው፡፡ 60 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ዝርጋታም የፕሮጀክቱ አንድ አካል ተደርጎ ይተገበራል፡፡ ፕሮጀክቱ የጎርፍ አደጋን ለመከላከል፣ ጤናማ፣ ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀ የመኖሪያ ከባቢን ዕውን ለማድረግም ያግዛል” ብለዋል፡፡

default

የአዲስ አበባ ለውጥ በኬንያ ብቻ ሳይሆን በደቡብ አፍሪካም በመልካም ተሞክሮነት ተነስቷል፡፡ ባለፈው ዓመት ለአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ አዲስ አበባ በተገኙበት ወቅት ከተማዋን ተዘዋውረው የመጎብኘት ዕድል ያገኙት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በአዲስ አበባ አስደናቂ ለውጥ በመደመም “ጆሀንስበርግ እንደ አዲስ አበባ እንድትሆን እንሠራለን” ማለታቸው ይታወሳል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፈው ነሐሴ ወር 2017 ዓ.ም “የመደመር መንግስት” የተሰኘውን አራተኛውን መጽሐፋቸውን በተመለከተ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ የተሰራው ልማት ለአፍሪካ ተምሳሌት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

“ምንም ጥርጥር የለውም፤ የኢትዮጵያ የወንዝ ዳርቻ ልማት ልክ እንደ አረንጓዴ አሻራ ለመላው አፍሪካ ምልክትና ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡” ያሉት ጠቅላይ  ሚኒስትሩ ገደልና የቆሻሻ መጠራቀሚያ የነበሩ የወንዝ ዳርቻዎች አሁን የተለየ ውበትና ገፅታ ይዘዋል፡፡ ለበርካታ ወገኖች የንግድና የስራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ የሀገርን ገፅታና መልክ መቀየራቸውን ተናግረዋል።

በቅርቡ በተካሄደው 39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህንን የሚያጠናክር ሀሳብ ሰጥተዋል። በአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ማልማት ስራ የተራቆቱ የወንዝ ዳርቻዎች ወደ ንፁህና እንቅስቃሴ የሞላባቸው የህዝብ መናፈሻ ቦታዎች ተቀይረዋል፡፡ የጎርፍ አደጋ ስጋትን መቀነስ፣ የሰዎችን ክብር ማስጠበቅና የማህበረሰቡን ህይወት ማጠናከር ተችሏል ነው ያሉት፡፡

ግሎባል ፒስ ባንክ በተሰኘ በሰላም ግንባታ ዙሪያ የሚሰራ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም የሰላም ግንባታና ፕሮሞሽን ዳይይሬክተር እና የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ አቶ ደያሞ ዳሌ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ሀሳብ፣ ኢትዮጵያ አፍሪካዊያን ከቅኝ ግዛት ለመውጣት ባደረጉት ትግል ቅኝ ባለመገዛት ተምሳሌት ከመሆን ባሻገር በገንዘብ፣ በስልጠና፣ በሞራልና በዲፕሎማሲም አይተኬ ሚና አድርጋለች፡፡ አፍሪካውያን ነጻነታቸውን እንዲያገኙና ወደ አንድነት እንዲመጡ የቀድሞውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት) በመመስረት ወሳኝ ሚና ተወጥታለች፡፡

default

ኢትዮጵያ አሁንም በታሪክ የነበራትን ሚና እያስቀጠለች እንደምትገኝ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ አቶ ዳያሞ ያነሳሉ። በቅርቡም በራሷ ሀብት፣ ጉልበትና አቅም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በመገንባት፣ በአረንጓዴ አሻራ ዛፍ በመትከል፣ አዳዲስ በጀመረቻቸው የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የጋዝ፣ የአየር ማረፊያ ግንባታና ሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በመገንባትና በመጀመር በኢኮኖሚ ረገድም አፍሪካዊያን ከብድርና እርዳታ ተላቅቀው በራሳቸው መቆም እንዲችሉ ተምሳሌት እየሆነች መጥታለች፡፡ እነዚህ ስራዎች አፍሪካውያን እርስ በእርስ ለማስተሳሰርና የኢኮኖሚ ውህደት ለማምጣት የሚያግዙም ናቸው፡፡

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ እንደሚሉት፣ የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ በከተማ ልማት እያሳየች ያለው ለውጥ የአፍሪካ መዲናነቷን የሚያጎለብትና ለሌሎች የአፍሪካ ከተሞች በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው፡፡ አዲስ አበባም ሆነ ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ምስረታ ፕላንን የተከተለ አይደለም፡፡ የአፍሪካ ህብረትና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ፣ በዓለም ሦስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል ብትሆንም ከዘመናዊ ከተማነት አኳያ ብዙ ጉድለቶች ነበሩባት፡፡

“አሁን ላይ በኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት ውብ፣ ፅዱና አረንጓዴ ከተማ ሆናለች” የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ አቶ ዳያሞ፣ ለምሳሌ የኬንያን ዋና ከተማ ናይሮቢን ብንወስድ ፅዱና ውብ የሆነ አካባቢ እንዳለ ሁሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙና ዜጎች የሚኖሩባቸው ያረጁ ሰፈሮች እንዲሁም የቆሸሹ ወንዞች ያሉባቸው አካባቢዎች አሉ፡፡ ደቡብ አፍሪካም በጣም ቆንጆ የሚባሉ ከተሞች ቢኖራትም ጥቁሮችና ደሃ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚኖሩባቸው የቆሸሹ አካባቢዎች ይገኛሉ፡፡ ከዚህ አኳያ በአዲስ አበባ በወንዝ ዳርቻ የተሰራው ልማት ለብዙ ከተሞች ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡ 39ኛውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ለመሳተፍ የመጡ የአፍሪካ መሪዎች ከአዲስ አበባ ተሞክሮ ለመውሰድ መልካም አጋጣሚ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review