የኮሪደር እና ወንዝ ዳር ልማት ወንጀልን ለመከላከል አይተኬ ሚና እንዳላቸው ተመላክቷል
ወጣት ቢንያም ወልዴ ይባላል። ከምሽቱ 1፡30 ሰዓት ገደማ ከሥራ አምሽቶ በመውጣት በተለምዶ መገናኛ “ማማስ ኪችን” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የአያት ጣፎ ታክሲ ለመያዝ ይሰለፋል። የታክሲ ሰልፉን ርዝማኔ ሲያይ ተስፋ በመቁረጥ “ቢያንስ አንድ ፌርማታ የሚያክል የእግር ጉዞ ባደርግ የአውቶቡስ ትራንስፖርት አማራጭ አገኛለሁ” በሚል በእግሩ መጓዝ ይጀምራል። ሆኖም ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ ለማመን የሚከብድ ነገር ይገጥመዋል።
ከኋላው አንድ ወጣት ‘የኔ ወንድም’ ብሎ ይጠራዋል። ዞር ሲል በጀርባው የያዘው ቦርሳ ዚፕ ክፍት እንደሆነ ይነግረዋል። ሐሳቡንም ቀልቡንም ወደ ቦርሳው ባደረገበት ቅጽበት፣ ከየት መጡ ሳይባል ሁለት ጎረምሶች ጉሮሮውን አንቀው በመያዝ ያለውን ንብረት በሰላም እንዲያስረክብ ይጠይቁታል። እሱም ያለበትን ሁኔታና የጎረምሶቹን ጭካኔ በመገንዘብ የተባለውን ሁሉ እንደፈጸመ ያስታውሳል። ይህን ማድረግ ባይችል በያዙት ጩቤ ወግተው ጨለም ወዳለ ስፍራ ወስደው እንደሚጥሉት እንደነገሩትና ከማድረግም እንደማይመለሱ በተሰበረ ስሜት አጫውቶናል።
በወቅቱ ሁለት ስልኮች፣ ስማርት ሰዓት፣ ታብሌት እና ጥቃቅን ንብረቶቹን ከመውሰዳቸው ባሻገር፣ ጉሮሮውን ጠፍንገው የያዙበት ቦታ ላይ ከፍተኛ የሕመም ስሜት እንደነበረበትና በዚህ ምክንያት ለሁለት ሳምንታት ድምፅ አውጥቶ ለማውራት ይቸገር እንደነበር ያስታውሳል።
ቀደም ባሉት ጊዜያት የመንገድ ዳር መብራቶች በተለያዩ ምክንያቶች ከአገልግሎት ውጪ መሆን፣ የመብራት መጥፋት እንዲሁም ከነአካቴው ማታ ላይ ብርሃን አለመስጠት አዝማሚያዎች በስፋት በመከሰታቸው፣ ለእንደዚህ ዓይነት የወንጀል ጥቃቶች ምቹ ሁኔታ ሲፈጥሩ መቆየታቸውን የሚገልጸው ወጣት ቢንያም፤ “ይህ ሁኔታ በእኔ ብቻ የደረሰ አይደለም፤ የተለያዩ የቅርብም ሆነ የሩቅ ሰዎች መሰል አደጋ ደርሶባቸው ያውቃሉ” ብሏል።

አሁን ላይ ጨለማን ተገን አድርጎ ወንጀል የሚፈጸምበት ችግር በከፍተኛ ደረጃ ተቀርፏል። ምክንያቱም በኮሪደር ልማት ሥራዎች አማካኝነት አሁን ላይ አዲስ አበባ ውስጥ በምሽት እንደልብ የመንቀሳቀስ አዝማሚያ በስፋት ይስተዋላል። ሰዎችም የእግር መንገድ ካደረጉ በኋላ ቢደክማቸው አረፍ በማለት ጥሩ ነፋሻማ አየር እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። ከዚህ በተጨማሪ “ሌባ ከኋላዬ ያዘኝ አልያዘኝ” የሚለው ሥጋት እንዳይፈጠር በየመንገዱ የተገጠሙ የደህንነት ካሜራዎች የደህንነት ስሜት እንዲሰማቸው እንዳደረጋቸውም አክሏል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ባዩሽ አንዷለም ይባላሉ፤ ነዋሪነታቸው ሰሜን ሆቴል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት፣ ጨለማን ተገን ያደረገ ወንጀል ተፈጽሞባቸው እንደሚያውቅ ነግረውናል። እሳቸው እንዳስረዱት ሁነቱ የተከሰተው ከዛሬ አራት ዓመት በፊት ነበር። የወለደች ልጃቸውን ለማረስ ቦሌ ሩዋንዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መመላለስን የዕለት ተዕለት ተግባራቸው አድርገውት ነበር። ታዲያ የተለያዩ የትራንስፖርት አማራጮችን በመጠቀም ወደ ቤታቸው ለመመለስ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ የእግር መንገድ ጉዞ ማድረጋቸው ግድ ይላቸው ነበር።
በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በነበራቸው የተደጋገመ ምልልስ የደረሰባቸውን አጋጣሚ ሲያስታውሱ፦ “ለአይን ያዝ ሲያደርግ ሀገር ሰላም ብዬ ከልጄ ቤት ወደ ትራንስፖርት መያዣ ስፍራ እያቀናሁ እያለ፣ ፈርጠም ፈርጠም ያሉ ወጣቶች የዝርፊያ ጥቃት አደረሱብኝ። ድርጊቱን የፈጸሙብኝ ጉሮሮዬን በማነቅ ምንም ዓይነት ድምፅ እንዳላሰማ ካደረጉ በኋላ ነው። ቦርሳዬ ውስጥ ያለውን ገንዘብ ለትራንስፖርት እንኳን ሳያስቀሩ በማውጣት፣ ስልኬንና የወርቅ ቀለበቴን ከጣቴ ላይ በማውለቅ ዘረፋ ፈጸሙብኝ። ይህን ሲያደርጉ የተጠቀሙት ኃይልና ጉልበት ራሴን እስከመሳት አድርሶኝ ነበር። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ራሴን ሳውቅ ከአንድ ጥግ ወድቄ አገኘሁት። ሕልምም መሰለኝ። ለመጮህ ፈለግሁ፤ ነገር ግን ጉሮሮዬ ላይ ያለው የሕመም ስሜት እንዳልጮህና ድምፅ እንዳላወጣ አስቸገረኝ። ራሴን ለማረጋጋት ሞከርኩ። በደረሰብኝ ወንጀል አዝኜ፣ ለልጄም ሳልነግር ከተሳፋሪዎች የታክሲ ገንዘብ ለምኜ ወደ ቤቴ አቀናሁ” በማለት በቅጽበት ውስጥ የተፈጸመባቸውን ከባድ ወንጀል አስታውሰዋል። “አሁን ላይ በተከናወነው የኮሪደር ልማት ምሽቱን እንደ ቀን ያደመቁ መብራቶች እንዲኖሩ ተደርገዋል። ይህም ሰዎች ያለምንም ሥጋት እንዲንቀሳቀሱ ዕድል ፈጥሯል” ሲሉ ሐሳባቸውን አጋርተዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ እንደአወቀ መስፍን በተለይ በወንዝ ዳርቻዎች አካባቢ ከዝርፊያ አንስቶ እስከ ነፍስ ማጥፋት የደረሰ ጥቃት በነዋሪዎች ላይ ይፈጸም እንደነበር አንስተዋል። እንደ ማሳያ ባነሱት ሐሳብ ላይ እንዳስረዱት፣ አንዱ ወዳጃቸው በጀርባው ያነገበውን ቦርሳ ላፕቶፕ መስሏቸው መንጭቀው አፍንጮ በር ተብሎ በሚጠራው የወንዝ ዳርቻ ዘልቀው በመግባት እንደተሰወሩባቸው አስረድተዋል። አሁን ላይ ግን ወንዞቻችን ታክመው የሌቦች መደበቂያ ከመሆን ይልቅ የመዝናኛ አማራጮች መሆን በሚችሉበት መልኩ መልማታቸው ትልቅ እፎይታን ፈጥሯል። አሁን ላይ ወንዝ ዳርቻዎች ሲደርስ የነበረው ወንጀል በመቀረፉ፣ ሰዓት ሳይመርጡ ለመንቀሳቀስ እንዳስቻሉ በመግለጽ ይህ ልማት እያበረከተ ያለውን ፋይዳ አብራርተዋል።

የዜጎችን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ከሚያውኩ ተግባራት መካከል አንዱ ዝርፊያ፣ ነፍስ ማጥፋት እና መሰል የወንጀል ድርጊቶች ስለመሆናቸው የሚናገሩት የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል መከላከል ዋና መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ገዛኸኝ ጌታነህ ናቸው። ወንጀል የሚፈጽሙ አካላት ይህን ድርጊት ለመፈጸም ምቹ የሆነ ጊዜና ሁኔታን ይመርጣሉ። አዲስ አበባ ከተማ ቀድሞ የነበራት ገጽታ ለጸጥታ ሥራ ምቹ የምትባል አልነበረችም። እንደ ሀገር እየተሠሩ ያሉ እንደ ኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች የከተማዋን ጸጥታ በማስጠበቅ ረገድ አይተኬ ሚና እያበረከቱ መሆኑን አብራርተዋል።
ከላይ የተጠቀሱት የልማት ሥራዎች ከመከናወናቸው በፊት በምሽት ጊዜ በተለይ የመንገድ መብራት በተበላሸባቸው አልያም በሌለባቸው አካባቢዎች ዝርፊያ፣ የነፍስ ማጥፋት እንዲሁም መኪኖች ሰዎችን ገጭተው የማምለጥ አዝማሚያ ይታይ ነበር። የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ በየጎዳናው ባሉ መብራቶች ላይ የደህንነት ካሜራዎች መገጠማቸው “ለእኛም ሥራዎችን በእጅጉ አቅልሎልናል” ሲሉ ተናግረዋል።
“የደህንነት ካሜራ መረጃዎችን በመጠቀም ወንጀል የሚፈጽሙ አካላትን አድነን የምንይዝበት አግባብ አለ” የሚሉን ኮማንደር ገዛኸኝ፣ አንድ አሽከርካሪ በሰው ሕይወት ላይ አደጋ አድርሶ ከአካባቢው ቢሰወር እንኳ የመኪናው ሰሌዳ ከካሜራዎቹ እይታ አያመልጥም ብለዋል። አንዳንድ ሰፈሮች የወንጀል መንስኤ የመሆን ዕድላቸው ሰፊ ነው። በተለይ እንደ ካሳንቺስ፣ አራት ኪሎ፣ ፒያሳ የመሳሰሉት አካባቢዎች ሺሻ ቤት፣ አረቄ ቤት እንዲሁም ሴተኛ አዳሪዎች በስፋት ይገኙባቸውና ይህን ተከትሎ ለወንጀሎች መጠንሰስና መፈጸም ምንጮች ነበሩ። የእጅ ቦርሳ ስርቆት፣ የሞባይል ስልክ ንጥቂያ፣ የላፕቶፕ፣ የእጅና የአንገት ጌጥ ዝርፊያ፣ የመኪና ስፖኪዮ እና መሰል ቁሳቁሶችን የመስረቅ አዝማሚያ በስፋት ይስተዋል ነበር። ወንጀለኞች ጨለማን ተገን አድርገው ዝርፊያ ሲፈጽሙ በሚኖረው ትንቅንቅ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ይደርስ ነበር። ወንጀለኞች ሰርቀው እንደ መሸሸጊያ የሚጠቀሙባቸው አካባቢዎች የወንዝ ዳርቻዎችን እንዲሁም መንደሮችን በመሆኑ ሳቢያ ለፖሊስም ጭምር አስቸጋሪ ሁኔታ ይፈጠር እንደነበር አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የፍትሕ እና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያን የ2018 ዓ.ም የ6 ወር ሥራ አፈጻጸሙን በገመገመበት ወቅት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የወንጀል መከላከል እና መቆጣጠር ሥራው ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን አሳውቋል። እንደ መረጃው ከሆነ የሕብረተሰቡ ሥጋት ናቸው ተብለው የተለዩ ከባድ ወንጀሎችን ለመቆጣጠር በተሠራ ሥራ፣ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 6 ወራት የተመዘገበው ውጤት ከ2017 ዓ.ም የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ46 ነጥብ 3 በመቶ ወንጀልን መቀነስ ተችሏል። ለውጤቱ መሳካት አስተዋጽኦ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል የኮሪደር ልማት ሥራው አይተኬ ሚና እንዳለው ተመላክቷል።
እንደ ኮማንደር ገዛኸኝ ገለጻ፣ ከዚህ ቀደም የወንዝ ዳርቻዎች የወንጀለኞች መሸሸጊያ እና ማምለጫ ሆነው ለበርካታ ዓመታት ቆይተዋል። አሁን ግን ወንዞችን ተገን ያደረገ የወንጀል ድርጊት ሙሉ ለሙሉ ቀርቷል። ከተማው ላይ ያሉ መብራቶች ምሽቱን ሙሉ ብሩህ ድባብን የፈጠሩ በመሆናቸው ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ተችሏል። ሰዎች ተቻኩለውና በሥጋት ውስጥ ሆነው የምሽት እንቅስቃሴ ከማድረግ ይልቅ የመዝናናትና ጥሩ ጊዜ የማሳለፍ ባሕል እያዳበሩ ይገኛሉ።
በሄለን ጥላሁን