በእግር ኳስ ዓለም ውስጥ መደበኛ ጨዋታዎች አሉ፤ ደግሞ ደም የሚያሞቁና ታሪክን በሁለት ጎራ ከፍለው የሚያፋልሙ የ‘ደርቢ’ ጨዋታዎች አሉ። ለብዙዎች እግር ኳስ መዝናኛ ሊሆን ይችላል፤ የ‘ደርቢ’ ፍልሚያዎች ግን ትርጉማቸው ብዙ ነው። የ‘ደርቢ’ ጨዋታዎች በሚካሄዱበት ዕለት ውጥረቱ ከሜዳ ይሻገራል፤ ጎረቤት ከጎረቤቱ ይኳረፋል፤ አባትና ልጅ ለ90 ደቂቃ እግር ኳሳዊ ባላንጣ ይሆናሉ።
‘ደርቢ’ ማለት የአንድ ከተማ ደጋፊዎች በሁለት ተለይተው “ይህች ከተማ የኔ ናት” የሚሉበት የክብር መድረክ ነው። ተጫዋቾች ያልፋሉ፤ አሰልጣኞች ይቀየራሉ፤ ስታዲየሞች እንኳ ሊፈርሱ ይችላሉ። ነገር ግን የአንድ ‘ደርቢ’ ድል የሚሰጠው ኩራትና ሽንፈቱ የሚያስከትለው የቅስም ስብራት ለትውልድ የሚሻገር ጠባሳ ጥሎ ያልፋል።
በዚህ አምድ ኳስ ከክብነቷ ወጥታ የሰው ልጅ ስሜት መተንፈሻ ወደምትሆንባቸው፣ ዓለምን ወደሚያስደንቁ ታላላቅ የ‘ደርቢ’ ፍልሚያዎች እንጓዛለን። መነሻችንንም ቱርኪዬን በማድረግ የ‘ደርቢ’ ፍልሚያዎችና ደጋፊዎች ስላላቸው ቁርኝት እንቃኛለን፡፡
ለመሆኑ አንድን ጨዋታ ‘ደርቢ’ የሚያሰኘው ምንድነው? ቅርበት ወይስ ጥላቻ? ለዚህ መሰረታዊ ጥያቄ ምላሽ እናገኝ ዘንድ መነሻችንን ኢስታንቡልን እናድርግ፡፡ በእግር ኳስ ውስጥ ስታዲየሞች የጨዋታ ሜዳ ብቻ አይደሉም፤ በተለይ በቱርክዬ ምድር ስታዲየም ማለት የክብር መለኪያ፣ አስደማሚ የድጋፍ ድባብና ተጋጣሚ ቡድኖችን ቅስማቸውን የሚሰብር ስፍራ ነው። የቱርክዬ ደጋፊዎች ለእግር ኳስ ያላቸው ፍቅር ከመደበኛው ስፖርታዊ ድጋፍ አልፎ ወደ ከባድ ሱስ ተቀይሯል።
ታላላቆቹ ሦስት ክለቦች ማለትም ጋላታሳራይ፣ ፌነርባቼ እና ቤሽክታሽ ደርቢ የሆኑበት ምክንያት ከኳስ ጨዋታ ባለፈ ማህበራዊ መደብ፣ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ እና ታሪካዊ ማንነት ላይ የተመሰረተ ስለመሆኑ የዘ ጋርዲያን ዘገባ ያትታል።
የኢስታንቡል ከተማ በቦስፎረስ ባህር ሰርጥ ለሁለት ስትከፈል አንደኛው ወገን አውሮፓ፣ ሌላኛው ደግሞ እስያ ነው። ጋላታሳራይ በአውሮፓው ክፍል የተመሰረተ ሲሆን፣ ፌነርባቼ ደግሞ በእስያ ክፍል ይገኛል። ይህ በመሆኑም በመካከላቸው የሚደረገው ጨዋታ ‘የአህጉራት ደርቢ’ የሚል ስያሜ እንዲያገኝ አስችሎታል። ደጋፊው ጨዋታውን የሚያየው እንደ አንድ ከተማ ቡድኖች ሳይሆን፣ እንደ ሁለት የተለያዩ ዓለማት ፍልሚያ አድርጎ ነው።
በሌላም በኩል ክለቦቹ ሲመሰረቱ የነበራቸው የደጋፊ መሰረት የተለያየ መደብ የነበረው ሲሆን፣ የጋላታሳራይ እግር ኳስ ክለብ የተመሰረተው በጋላታሳራይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሲሆን፣ በወቅቱ የነበሩት ደጋፊዎች የተማሩ፣ የምዕራባውያን አስተሳሰብ ያላቸውና የሀብታሙ መደብ አባላት ነበሩ። የፌነርባቼ እግር ኳስ ክለብ እንደዚሁ የተመሰረተው በሰራተኛውና በነጋዴው ማህበረሰብ በመሆኑና ‘የህዝብ ቡድን’ ተብሎ ስለሚታመን፣ ከማንኛውም የፖለቲካ ወይም የኢኮኖሚ ተጽዕኖ ነፃ የሆነ የብዙሃኑ ድምጽ ተደርጎ ይወሰዳል።
ወደ ኢስታንቡል የሚጓዙ የአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች ተጫዋቾች ታዲያ ገና አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የሚቀበላቸው መፈክር “እንኳን ወደ ሲኦል በደህና መጡ” (Welcome to Hell) የሚል ነው። ይህ ማስፈራሪያ ብቻ አይደለም፤ በስታዲየም ውስጥ የሚለኮሱት በመቶዎች የሚቆጠሩ የጭስ ችቦዎች ስታዲየሙን ቀይ እሳት ያስመስሉታል። የቱርክ ደጋፊዎች በጩኸት ከፍተኛውን የ‘ዴሲቤል’ (Decibel) መጠን በመመዝገብ የዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ወይም ‘ጊነስ ሪከርድ’ን ደጋግመው ሰብረዋል። ድምፁ በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ተጫዋቾች በሜዳ ላይ ጎን ለጎን ቆመው መነጋገር አይችሉም እስከመባል ተደርሷል።
ቢቢሲ የኢስታንቡል ‘ደርቢ’ን “በዓለም ላይ ካሉ እጅግ አስፈሪ እና ስሜታዊ እግር ኳስ ፍልሚያዎች አንዱ” ሲል ዘግቦታል። በተለይ በደጋፊዎች የሚፈጠረውን የድምፅ መጠን እና ስታዲየሞች ውስጥ የሚታየውን የእሳት ጭስ “ከእግር ኳስ ጨዋታ በላይ የሆነ ትርኢት” በማለት ይገልጸዋል።
የቱርክዬ እግር ኳስ ማማ ላይ ያሉት ጋላታሳራይ እና ፌነርባቼ ሲሆኑ፣ ይህ ጨዋታ ሲደርስ መላው ቱርክ ለሁለት ትከፈላለች። በ‘ደርቢ’ው ቀን በኢስታንቡል ጎዳናዎች ላይ እንቅስቃሴ ይቆማል። ደጋፊዎች ቡድናቸው ከተሸነፈ እስከ ቀጣዩ ጨዋታ ድረስ አንገታቸውን ደፍተው ነው የሚኖሩት። ድሉ ግን የሳምንታት ብሔራዊ በዓል ያህል ይከበራል።
እግር ኳስ 90 ደቂቃ ብቻ አይደለም፤ የቤሽክታሽ ደጋፊ ልጁ ሲወለድ መጀመሪያ የሚያደርገው የቡድኑን ማሊያ ማልበስ ነው። በቅርቡ እውቁ አሰልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆ ወደ ፌነርባቼ ሲመጡ የተደረገላቸው አቀባበል የቱርክዬ ደጋፊዎች ምን ያህል ለስፖርቱ ፍቅር እንዳላቸው ያሳይ ነበር። በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች ስታዲየም ተገኝተው ለአሰልጣኙ የሰጡት አቀባበል ለብዙ ሀገራት ለዋንጫ ድል የሚሰጥ ዓይነት ነበር። ለዚህም ነው ብዙ ኮከብ ተጫዋቾች በደመወዝ ማነስ እንኳ ሳይገደቡ ያንን ‘የእብደት’ ድባብ ለመቅመስ ወደ ቱርክዬ የሚያመሩት።
የስፖርት ተንታኞችና የስነ-ልቦና ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ የቱርክዬ ‘ደርቢ’ዎች ወይም ሌሎች ዓለም አቀፍ የ‘ደርቢ’ ፍልሚያዎች ከስፖርታዊ ውድድር ባለፈ ጥልቅ ማህበራዊ ትርጉም አላቸው። በቱርክ ስፖርት ስነ-ልቦና ላይ ጥናት ያደረጉት የስነ-ልቦና ባለሙያው ሜህመት ኦዝካን (ዶ/ር)፣ “ለብዙ የቱርክዬ ደጋፊዎች ክለባቸው ማለት ቤተሰባቸው ነው። በኑሮ ውስጥ የሚገጥሟቸውን ውጥረቶችና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች የሚረሱት በስታዲየም ውስጥ በሚያወጡት ጩኸት ነው። እዚያ ውስጥ ‘እኔ’ የለም፤ ‘እኛ’ ብቻ ነው ያለው። ያ ደግሞ ለሰው ልጅ ትልቅ የደህንነትና የማንነት ስሜት ይሰጠዋል” ይላሉ፡፡
የቀድሞው የጋላታሳራይ ተጫዋችና የአሁኑ የስፖርት ተንታኝ ሀካን ኡንሳል ስለ ‘ደርቢ’ዎቹ ግለት ሲያስረዳ፣ በቱርክዬ ‘ደርቢ’ መሸነፍ ማለት ለሚቀጥሉት ወራት አንገት ደፍቶ መሄድ ማለት ነው። ደጋፊው ተጫዋቾቹ እንዲያሸንፉ የሚፈልገው ስለ ዋንጫው ብቻ ሳይሆን፣ በከተማዋ ላይ ስላለው ‘የበላይነት ኩራት’ ጭምር ስለመሆኑ ያስረዳሉ፡፡ አክለውም፣ በሜዳ ላይ ያለው ጫና ተጫዋቾችን ወይ ጀግና ያደርጋቸዋል፣ ወይም ሙሉ በሙሉ ያጠፋቸዋል ብለዋል፡፡
ከቱርኪዬ ባሻገር፣ በአርጀንቲና የሚካሄደው የቦካ ጁኒየርስ እና የሪቨር ፕሌት ‘ሱፐር ክላሲኮ’ የዓለም እግር ኳስን ትኩረት የሚስብ እጅግ ግዙፍ ‘ደርቢ’ ነው። በቦነስ አይረስ ከተማ የሚገኘው የቦካ ጁኒየርስ ስታዲየም ‘ላ ቦምቦኔራ’ ደጋፊዎቹ በጋራ ሲዘልሉ የመሬት መንቀጥቀጥ ያህል እንደሚርገበገብ ይነገራል። እዚህ ደርቢ ላይ ኳስ ጨዋታ ብቻ ሳትሆን የክብርና የማንነት መገለጫ ነች፤ ደጋፊዎቹ በሚፈጥሩት ባለቀለም ወረቀቶችና የጭስ ድባብ ሜዳው ለተመልካችም ሆነ ለተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች እጅግ አስፈሪና አስደሳች ድባብን ይፈጥራል።
‘ኦልድ ፊርም’ በሚል መጠሪያ የሚታወቀው የስኮትላንዱ የሴልቲክ እና ሬንጀርስ ፍልሚያ ታሪካዊ ‘ደርቢ’ በታሪክ፣ በኃይማኖትና በፖለቲካዊ ልዩነቶች የታጀበ በመሆኑ በዓለም ላይ ካሉ እጅግ ጠንካራ ‘ደርቢ’ዎች መካከል አንዱ ነው። በግላስኮ ከተማ የሚካሄደው ይህ ፍልሚያ ደጋፊዎቹ ለ90 ደቂቃ ሳይታክቱ በሚያሰሟቸው መዝሙሮችና ጩኸቶች ይታወቃል። በተመሳሳይ የጀርመኑ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ደጋፊዎች የሚፈጥሩት ‘ቢጫው ግንብ’ (The Yellow Wall) በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች በአንድ ላይ ቆመው የሚፈጥሩት አስገራሚ ትርኢት፣ እግር ኳስ ከስፖርታዊ ውድድር ባለፈ እንዴት ያለ ጥልቅ ስሜትና ጥበባዊ ድባብ ሊኖረው እንደሚችል ለዓለም የሚያሳይ አብነት ነው።
ባለሙያዎች እንደሚስማሙበትና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንም ደጋግመው እንደዘገቡት፣ የቱርክዬ ‘ደርቢ’ዎችም ሆኑ የዓለም ታላላቅ የከተማ ፍልሚያዎች ከ90 ደቂቃ ጨዋታ በላይ ናቸው። እነዚህ ጨዋታዎች የሰው ልጅ ለማንነቱ፣ ለክብሩና ለሚወደው ስብስብ ያለው ታማኝነት የሚገለጥባቸው መድረኮች ናቸው። በኢስታንቡል ድምፅ የሚያደነቁረው ጩኸት፣ በቦነስ አይረስ የሚርገበገበው ስታዲየም፣ ወይም በግላስኮ የሚሰማው ጥልቅ መዝሙር ሁሉ የሚያረጋግጡት እውነት አለ። በአንድ በኩል እግር ኳስ ውበት የሚኖረው በሜዳው ላይ በሚታየው ጥበብ ብቻ ሳይሆን፣ በተመልካቹ ደም ውስጥ በሚፈሰው ስሜት ጭምር ነው። በሌላም በኩል ‘ደርቢ’ዎች የሚነግሩን ትልቁ ቁም ነገር እግር ኳስ ቋንቋ፣ ኃይማኖትና ድንበር ሳይገድበው ሰዎችን በአንድ ስሜት የማስተሳሰር ትልቅ ኃይል እንዳለው ነው፡፡