AMN – የካቲት 14/2018 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከውጭ የሚገባን ምርት በመተካት 849 ነጥርብ 4 ሚሊዮን ዶላር ማዳን መቻሉን የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ገለጹ፡፡
ወጪ ምርት ላይ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች የሚያስገኙት ዶላር መሻሻል እያሳየ መምጣቱንም አቶ ጀንጥራር ተናግረዋል፡፡
በስድስት ወራት ውስጥ በመዲናይቱ ከሚገኙ ኢንደስትሪዎች ከወጪ ንግድ 127 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን እና ገቢ ምርትን በመተካት ደግሞ 849 ነጥርብ 4 ሚሊዮን ዶላር ማዳን መቻሉን ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊው አቶ ጃንጥራር አባይ ገልጸዋል፡፡
በመዲናይቱ ግራናይት፣ ፒቪሲ ምርቶች፣ ቧንቧና ከቧንቧ ጋር የተያያዙ ፕላስቲክ ምርቶች፣ ኮንዲዩቶች የመሳሰሉ የኤሌክትሪክ ገመዶች እየተመረቱ እንደሚገኝ ከኤ ኤም ኤን ዘጋቢ ጋር ባደረጉት ቆይታ ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን በመከተል በአዲስ አበባ የአምራች ኢንደስትሪዎች ችግሮች እየተፈቱ፣ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ፣ የአምራች ኢንደስትሪው ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንም አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአዲስ አበባ ዘንድሮ አምስተኛ አመቱ ላይ ደርሷል፡፡
ንቅናቄው አንድ የአደባባይ ሁነት ተደርጎ መወሰድ የለበትም የሚሉት አቶ ጃንጥራር፣ ላለፉት ጊዜያት በተከናወነው ስራ ብዙ ለውጦች መታየታቸውን ተናግረዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ቁጥሮች እንዲጨምሩ መደላድል መፍጠሩንና አሁን ላይ ወደ 3 ሺህ 878 አካባቢ የሚሆኑ ኢንዱስትሪዎች በአዲስ አበባ በስራ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ኢንዱስትሪዎቹ በአነስተኛ፣ በመካከለኛና በከፍተኛ ውስጥ ተካተው የሚገኙ ናቸው፡፡
በታደሰ ሽፈራው