AMN – የካቲት 14/2018ዓ.ም
ለኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች ዓለም አቀፍ የትምህርት ዕድሎችን እና ስኮላርሺፕ ማመቻቸት ላይ ትኩረት ያደረገ የሳይንስና ትምህርት የወጣቶች ፌስቲቫል በዓድዋ ድል መታሰቢያ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
ኢትዮ – ዓለም አቀፍ የወጣቶች የትምህርትና ቴክኖሎጂ ፌስቲቫል ለኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች ዓለም አቀፍ የትምህርት ዕድሎችን እና ስኮላርሺፕ ማመቻቸት ላይ ትኩረት አድርጎ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ፓን አፍሪካ አዳራሽ እየተካሄደ ነው።
ከየካቲት 14 እስከ 15 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የሚቆየው ዓለም አቀፍ የሳይንስና ትምህርት የወጣቶች ፌስቲቫል ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች ከ100 በላይ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎችና የትምህርት ተቋማት ጋር ትስስር መፍጠር የሚችሉባቸውን መረጃ ማቅረብ፣ የትምህርት ዕድል ፍለጋ እና የምዝገባ ሂደቶችን ማቃለል የፌስቲቫሉ አላማ ነው ተብሏል።
ካናዳ እና አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ዩኒቨርስቲ ተወካዮች በተቋሞቻቸው ያሏቸውን አማራጮች አስተዋውቀዋል፡፡
ፌስቲቫሉ ወጣቶችን ከዓለም አቀፍ የዕውቀት ዑደት ጋር የሚያገናኝ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መድረክ ሆኖ እንደሚያገለግል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
በካሳሁን አንዱዓለም