AMN – የካቲት 15/ 2018ዓ.ም
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሕጻናት የሚከሰተውን ኦቲዝምና የአእምሮ መዛባት መንስኤውን ማስወገድ የሚያስችሉ ሁለት የዘረ-መል ህክምና ፕሮጀክቶችን ማስጀመሯ ተዘገበ፡፡
የኤምሬቶች ጤና አገልግሎት ይፋ ያደረጋቸው የዘረ መል ሕክምና ፕሮጀክቶች ምልክቶቹን ለመቆጣጠር ከመሞከር ፍቱን ህክምና ወደ መስጠት የሚያሸጋግር ሊሆን ይችላል የሚል ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዕቅድ ፣ የዘረ-መል አወቃቀርን በመጠቀም ታማሚዎችን ማከም ሳይሆን ቀድሞኑ ይህ መዛባት እንዲፈጠር ምክንያት የሆነውን ባይሎጂያዊ ንድፍ ሁኔታ መጠገንን ዒላማ ያደረገ መሆኑን ነው ታይምስ ኦፍ ኢንድያ የዘገበው፡፡
እጅግ ፈር ቀዳጅ ነው የተባሉት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሁለቱ የዘረ-መል ህክምና ፕሮጀክቶች ውስብስብ የሆነው የህጻናት የነርቭ እና ዘረ-መል ሁኔታን ማከም ላይ ያተኮረ እንደሆነ ተዘግቧል፡፡
ጥረቱ ከተለለመደው ምልክት ተኮር እንክብካቤ ወደ መሰረታዊው የበሽታው የዘረ-መል መንስኤን ወደ ማስቀረት በማሸጋገር የነርቭ ጤና እንክብካቤ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ተብሏል፡፡
አንደኛው ፕሮጀክት ከኦቲዝም እና የሚጥል በሽታ ዘረ-መላዊ ምክንያቶች ላይ የሚያተኩር ሲሆን ከፊላዴልፊያ የሕጻናት ሆስፒታል ጋር በትብብር እየበለጸገ እንሚገኝ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
ሁለተኛው ፕሮጀክት የነርቭ መጎዳት ወይም መመናመን በሽታ ላይ ማዕከል እንደሚያደርግ ነው የተጠቀሰው፡፡ ተመራማሪዎች ጉድለት የታየባቸውን ዘረ-መሎች መጠገን የሚቻልባቸውን አማራጮች ይፈትሻሉ ተብሏል፡፡
ታደሰ ሽፈራው