AMN – የካቲት 15/2018 ዓ.ም
የንግድ ተወዳዳሪነትን በማስከበርና አስተማማኝ የምርት አቅርቦትን እውን በማድረግ ረገድ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ሚና የላቀ መሆኑ ተገለጸ።
አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በዐቢይ እና ረመዳን ጾም ሳምንታት የቅዳሜና እሁድ ግብይት ቅኝት አድርጓል።
በገበያ ቦታዎቹ የሚገኙ ነጋዴዎችና ሸማቾች እንደገለጹት፣ ምርቶች በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕብረተሰቡ እየቀረቡ ይገኛሉ ብለዋል።
የግብይት ሁኔታው እጅግ አበረታች መሆኑን የገለጹት ሸማቾች፣ ማንኛውም ሰው እንደ አቅሙና እንደ ምርጫው መርጦ የሚገዛበት ሰፊ አማራጭ መኖሩን ተናግረዋል።
ግብይቱ መንግሥት ባወጣው የዋጋ ተመን መሠረት እየተከናወነ ስለመሆኑና ጥብቅ የክትትልና የቁጥጥር ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ተቆጣጣሪዎቹ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የዋጋ ጭማሪም ሆነ የምርት ጥራት ችግር በሚያጋጥምበት ወቅት ሕብረተሰቡ ጥቆማ የሚያደርስበት ስልክ መኖሩን የገበያ ተቆጣጣሪዎች ገልፀዋል፡፡
የገበያ ትስስርን በማጠናከርና አማራጭ የገበያ ዕድልን በመፍጠር ረገድ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ሕብረተሰቡን ከተለያዩ የኢኮኖሚ ጫናዎች እየታደጉ እንደሚገኙ ሸማቾችና ነጋዴዎች ተናግረዋል።
በቅዳሜና እሁድ ገበያዎቹ የሚታየው ዋጋ ከመደበኛ ሱቆች ጋር ሲነጻጸር ከ10 እስከ 15 ብር ድረስ ቅናሽ እንዳለው በቅኝቱ ለመታዘብ ተችሏል።
በበረከት ጌታቸው