AMN – የካቲት 16/2018 ዓ.ም.
በአዲስ አበባ ከተማ በተያዘው የ2018 በጀት ዓመት ለመገንባት ከታቀዱ 100 ሺህ ቤቶች መካከል የ97 ሺህ ቤቶች ግንባታ በተፋጠነ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።
ከንቲባዋ ዛሬ በማለዳ በከተማዋ በተለያዩ ሳይቶች እየተከናወኑ ያሉ የቤት ልማት ፕሮጀክቶችን የመስክ ምልከታና ግምገማ ማካሔዳቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አጋርተዋል።
ከንቲባዋ እንዳሉት በከተማዋ እየተካሔደ ያለው ዘርፈ ብዙ የልማት እንቅስቃሴ ለቤት ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቷል። በመስክ ምልከታቸውም በገርጂ፣ በቱሉ ዲምቱ፣ በገላን ጉራ (የመጀመሪያና ሁለተኛ ምዕራፍ)፣ በአቃቂ ቃሊቲ ወርቁ ሰፈር እንዲሁም በንፋስ ስልክ ላፍቶ የገበያ ማዕከል እየተገነቡ ያሉ ቤቶችን የሥራ ሒደት ገምግመዋል።
ግንባታቸው ከተጀመረ ከ6 እስከ 7 ወራት ብቻ ያስቆጠሩት እነዚህ ፕሮጀክቶች፣ በ24/7 የሥራ ባሕል፣ በትጉህ ኢትዮጵያውያን ኮንትራክተሮች፣ በማኅበራትና በአማካሪዎች ጥረት እንዲሁም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዘው በአሁኑ ወቅት አበረታች ደረጃ ላይ መድረሳቸው ገልጸዋል።

ይህ መጠነ ሰፊ የቤት ልማት እንቅስቃሴ ከ200 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን የገለጹት ከንቲባዋ የመንግስት ትኩረት የግንባታ ፍጥነት ላይ ብቻ ሳይሆን ጥራትን በማረጋገጥ ውብና ዘመናዊ የመኖሪያ መንደሮችን መገንባት መሆኑን አስታውቀዋል።
የግንባታ ጥራቱን የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በአማካሪነት አብሮ እየሠራ ሲሆን አሁን እየተገነቡ ካሉት ቤቶች መካከል 50 ሺዎቹ በከተማ አስተዳደሩ በጀት፣ ቀሪዎቹ 50 ሺህ ቤቶች ደግሞ በመንግስትና በግል አጋርነት (PPP) እየተከናወኑ መሆናቸውን አንስተዋል።
ከንቲባዋ ቀደም ሲል የነበረውን አሠራር በማስታወስ፥ “ከለውጡ በፊት እንዲህ አይነት ሰፊ የቤት ልማት በከተማው በጀት ቀርቶ በባንክ ብድር እንኳን በየአምስት ዓመቱ 100 ሺህ ቤቶች ተገንብተው ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ለረጅም ዓመታት ተመዝግበው ባልጠበቁና አስተዳደሩም የ60 ቢሊዮን ብር የኮንዶሚኒየም ቦንድ ዕዳ ባልተረከበ ነበር” ብለዋል።
ምንም እንኳን የቤት ፍላጎቱና አቅርቦቱ ገና ያልተመጣጠነ ቢሆንም፣ የቤት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት የሚከናወነው ተግባር ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከንቲባዋ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።