ከለዉጡ በፊት በአምስት አመታት ዉስጥ 100 ሺህ ቤቶች ቢገነቡ ኖሮ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ቤት ለመጠባበቅ፤ ከተማ አስተዳደሩም ከ60 ቢሊዮን ብር የሚበልጥ የኮዶሚንዬም የቦንድ እዳ ለመክፈል አይገደዱም ነበር

You are currently viewing ከለዉጡ በፊት በአምስት አመታት ዉስጥ 100 ሺህ ቤቶች ቢገነቡ ኖሮ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ቤት ለመጠባበቅ፤ ከተማ አስተዳደሩም ከ60 ቢሊዮን ብር የሚበልጥ የኮዶሚንዬም የቦንድ እዳ ለመክፈል አይገደዱም ነበር

AMN- የካቲት 17/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመዲናዋ ለአመታት የተከማቸዉን እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣዉን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማሟላት በተለያዩ መርሃ ግብሮች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ግንባታዎችን ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ በመታገዝ ጭምር በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

በመዲናዋ በመንግስትና የግል አጋርነት እንዲሁም በከተማው በጀት በዚህ አመት ሊገነቡ ከታቀዱ 100 ሺ ቤቶች መካከል 97 ሺህ ቤቶች ወደ ግንባታ ሂደት የገቡ ሲሆን ሁሉንም በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ይገኛል፡፡

በፍጥነት እየተገነቡ ካሉት ቤቶች ውስጥ 50 ሺዎቹ በከተማው በጀት የሚገነቡ ሲሆን የተቀሩት 50 ሺዎቹ ደግሞ በመንግስትና የግል አጋርነት የሚገነቡ ናቸዉ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በ17 ሳይቶች በግንባታ ላይ ካሉ ቤቶች መካከል በገርጂ፣ በቱሉ ዲምቱ፣ በገላን ጉራ (የመጀመሪያና ሁለተኛ ምዕራፍ)፣ በአቃቂ ቃሊቲ (ወርቁ ሰፈር) እንዲሁም በንፋስ ስልክ ላፍቶ የገበያ ማዕከል እየተገነቡ ያሉትን ቤቶች የስራ ክንዉን ገምግመዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ ከተጀመሩ ከ6 እስከ 7 ወራት ቢሆናቸዉም በ24/7 የሥራ ባህል እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ አፈጻጸማቸዉ አበረታች ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ ከ200 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም የስራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቤቶች ልማት ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ አበረታች ስራዎችን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልእክት ከለውጡ በፊት በተለመደዉ የባንክ ብድር በአንድ አመት ዉስጥ ቀርቶ በአምስት አመታት ዉስጥ 100 ሺህ ቤቶች ቢከናወኑ ኖሮ የመዲናዋን ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ችግር በዘላቂነት መፍታት ይቻል እንደነበር አንስተዋል፡፡

ነገር ግን ከለዉጡ በፊት በአምስት አመታት ዉስጥ 100 ሺህ ቤቶችን መገንባት ባለመቻሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ተመዝግበው ለረጅም አመታት ቤት ለመጠበቅ፣ የከተማ አስተዳደሩም ከ60 ቢሊዮን በላይ የኮዶሚንዬም የቦንድ እዳን ተረክቦ ለመክፈል እና ለማስተናገድ መገደዱን ገልጸዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ አሁን እየገነባን ያለነው ምንም እንኳን ከነዋሪዎቻችን ሰፊ ፍላጎት አንጻር አቅርቦቱ ገና ቢሆንም፣ የቤት ችግርን በዘላቂነት የመፍታት ስራችን ይበልጡን ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ መርሃ ግብሮች የሚያስገነባቸዉ የመኖሪያ መንደሮች በተሻሻለ ዲዛይን ጤናማ፣ ውብና ዘመናዊ ከመሆናቸዉም በላይ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የግንባታዉን የጥራት ደረጃ በማረጋገጥ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በአማካሪነት አብሮ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review