AMN- የካቲት 17/2018 ዓ.ም
በሀገራችን የመጀመሪያ የሆነውን የተንቀሳቃሽ የመሶብ አገልግሎት ለመጀመር ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የመሶብ አገልግሎት በቋሚነት ከሚሰጥበት ቢሮ በተጨማሪ ተንቀሳቃሽ ቢሮ እንደሚያስፈልገው መግለፃቸው ይታወሳል።
በዚህም መሰረት መሶብ አገልገሎት በአንድ ቢሮ ላይ ተወስኖ አገልግሎት በመስጠት ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን፣ በጣም ተደራሽነቱን ማስፋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የመሶብ አገልግሎት በተለያዩ አካባቢዎች በተንቀሳቃሽ ለመስጠት በአዲስ አበባ ደረጃ ወደ አገልግሎቱ ለመገባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ ገልፀዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የተንቀሳቃሽ አገልግሎት ጥቅሙ ብዙ መሆኑን በመግለፅ፣ ከምንም በላይ ጎልቶ የሚታየው ደግሞ አካታች የሆነ አገልግሎት መስጠት እንዲያስችል ሆኖ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመንግስት ተቋም ቀርበው አገልገሎት ለማግኘት የሚቸገሩ እና ከቤት መውጣት የማይችሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከአካበባቢያቸው ሳይርቁ ወዳሉበት ቀረብ ብሎ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት ለማድረግ ታሰቦ የተዘጋጀ መሆኑንም ነው የተናገሩት ።
ለተንቀሳቃሽ የመሶብ አገልግሎት የሚውሉ ትላልቅ ኤሌክትሪክ አውቶቡሶች መዘጋጀታቸውንና የዲዛይን ሥራም ተጠናቆ ወደ መካኒካል ሞዲፊኬሽን ሥራ መሸጋገሩን አቶ ዮናስ አለማየሁ አብራርተዋል።
አውቶብሶቹ በውስጣቸው የመሶብ ቢሮን የሚመስል ይዘት ኖሯቸው ሰራተኞች በአንድ ቦታ በርካታ አገልግሎቶችን መስጠት እንዲያስችል ሆኖ መዘጋጀቱም ተገልጿል።
በእርግጠኝነት ከሃያ እስከ ሃያ አምስት ቀናት ባሉ ጊዜያት ውስጥ አዲስ አበባ የመጀመርያውን ስማርት የመሶብ ተንቀሳቃሽ አገልግሎት ወደ ስራ ታስገባለች ሲሉም አቶ ዮናስ ገልፀዋል።
በያለው ጌታነህ