AMN- የካቲት 17/2018 ዓ/ም
ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ከ434 ሺህ በላይ የመኖሪያ ቤቶች ተገንብተው ለነዋሪዎች እንዲቀርቡ መደረጉንና የከተማ አስተዳደሩ ለነዋሪዎች የገባውን ቃል በተግባር እየተረጎመ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
ከንቲባዋ፤ የቤት ልማት ፕሮጀክቶችን የመስክ ምልከታ ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት፤ ቤቶቹ በተለያዩ የልማት አማራጮች የቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።
ከነዚህም መካከል ግንባታቸው ተጠናቆ በሁለት ዙር የዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓት ለተጠቃሚዎች የተላለፉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያደረገ አሠራርም ተዘርግቷል ብለዋል።
በዚህም መሠረት የግል ባለሀብቶች በሚያከናውኗቸው የቤት ልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ ዝቅተኛ ዋጋ ያላቸው ቤቶች ተካተው አቅም ለሌላቸው ነዋሪዎች እንዲቀርቡ መደረጉን ገልጸዋል።
በተጨማሪም አቅም ያላቸው ነዋሪዎች በተራዘመ የክፍያ ሥርዓት ከሪል ስቴት አልሚዎች ቤት ማግኘት እንዲችሉ መንግሥት የገበያ መረጋጋትን በመፍጠር ረገድ የጎላ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ከንቲባዋ አብራርተዋል።
ምንም እንኳን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቤቶች ቢገነቡም፣ አሁንም በሚሊዮን የሚቆጠር የቤት ጥያቄ መኖሩን ከንቲባዋ ገልጸው፣ በተለይም ከቀድሞው ሥርዓት ጀምሮ ተመዝግበው ቤት ሳይደርሳቸው የቆዩ ዜጎችን ችግር ለመፍታት አስተዳደሩ ዕዳውን ተረክቦ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
እነዚህን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ለማድረግ በመንግሥትና በግል አጋርነት የሚገነቡ ቤቶችን ለማስተላለፍ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንና ለተመዝጋቢዎች ቅድሚያ እንደሚሰጥም አረጋግጠዋል።
በአሁኑ ወቅት ግንባታ ላይ ያሉ የቤት ፕሮጀክቶች በጥሩ መነሳሳትና ጥራት ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ከንቲባዋ፣ የግንባታ ሂደቱን በቅርበት ለመከታተል ባለድርሻ አካላት በጋራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በሙያዊ ምክረ-ሐሳብ በመስጠትና በቴክኖሎጂ እያገዘ እንደሚገኝም ከንቲባ አዳነች አቤቤ አንስተዋል።
በበረከት ጌታቸው