በክህደት እና በበቀል የተገነባው የሰሜን ለንደን ባላንጣነት

You are currently viewing በክህደት እና በበቀል የተገነባው የሰሜን ለንደን ባላንጣነት

AMN- የካቲት 19/2018 ዓ.ም

በዓለማችን ላይ በርካታ የእግር ኳስ ባላንጣዎች ይገኛሉ፡፡ አርሰናል እና ቶትንሃም ወይም የሰሜን ለንደን ደርቢ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ውስጥ ካሉ ታላላቅ እና እጅግ የጦፈ ፉክክር ከሚታይባቸው ባላንጣዎች አንዱ ነው። ይህ የእግርኳስ ፉክክር ከስፖርታዊ ጨዋነት ባለፈ ታሪካዊ ፣ ጂኦግራፊያዊ እና ስሜታዊ መሰረቶች አሉት።

የጂኦግራፊያዊ ቅርበት ወይም የሰሜን ለንደን ይዞታ የባላንጣነት የመጀመሪያው ምክንያት ነው። መጀመሪያ አርሰናል ሲመሰረት ደቡብ ለንደን (ዉልዊች) ነበር ። ቶትንሃም ደግሞ በሰሜን ለንደን ብቸኛው ትልቅ ክለብ ሆኖ ለዓመታት ቆይቷል።

ነገር ግን በ1913 ዓ.ም አርሰናል ወደ ሰሜን ለንደን (ሀይበሪ) ተዛወረ። ይህም በቶትንሃም ደጋፊዎች ዘንድ “የእኛን መንደር ወረሩብን” የሚል ስሜት ፈጠረ።

የቶትንሃም ደጋፊዎች አርሰናልን እንደ መጤ ስለሚመለከቱት የሰሜን ለንደን ትክክለኛ ባለቤት እኛ ነን የሚለው ክርክር የጀመረው እዚህ ጋ ነው።

ቶትንሃም ሆትስፐርስ የተመሰረተው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1882 ሲሆን አርሰናል ደግሞ ከአራት ዓመት በኃላ በ1886 ነው፡፡ ይህም አንዱ መከራከሪያ ነጥብ ሲሆን ቶትንሃም ቀደምቶች እኛ ነን የሚል መከራከሪያ ቀርባሉ፡፡

ለዚህ ማሳያ ባለፈው እሁድ የቶትንሃም ሆትስፐር ደጋፊዎች (North London Since 1882) የሚል ባናር በትልቁ ስታድየም ይዘው መግባታቸው “እኛ ምድረ ቀደመት ነን” ለማለት እንደሆነ አስረጅ አያስፈልገውም፡፡

ሌላኛው የባላንጣነት መንስኤ ደግሞ የ1919ኙ አወዛጋቢ ውሳኔ ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ፣ የእንግሊዝ አንደኛ ዲቪዚዮን ቡድኖችን ከ20 ወደ 22 ከፍ ለማድረግ ተወሰነ።

አርሰናል በሊጉ ስድስተኛ ሆኖ ስለነበረ በሊጉ መጨረሻ ላይ ከነበረው ቶትንሃም ተመራጭ ሆኖ ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን እንዲያድግ ተደረገ። የቶትንሃም ደጋፊዎች አርሰናል በፖለቲካዊ ተጽዕኖ እንጂ በብቃቱ አይደለም ያለፈው ብለው ስለሚያምኑ ያ ቂም እስከ ዛሬ አልቀዘቀዘም።

ዘመናዊው ፉክክር ደግሞ በግል ጥላቻ የታጀበ ነው። በተጫዋቾች ዝውውር ረገድም ፉክክሩን የሚያባብሱ ነገሮች ተከስተዋል። ለዚህ ትልቁ ማሳያ የቶትንሃም አምበል የነበረው ሶል ካምቤል እኤአ በ2001 በነፃ ዝውውር ወደ ቀጥተኛ ባላንጣው አርሰናል ማምራቱ ነው። ይህም በቶትንሃም ደጋፊዎች ዘንድ እንደ ትልቅ ክህደት ተቆጥሮ “ይሁዳ” ሚል ስያሜ አሰጥቶታል፡፡ ካምቤል ከአርሰናል ጋር ዋንጫዎችን ሲያነሳ ፣ ጥላቻው ይበልጥ እየከረረ ሄደ።

አርሰናል ደጋፊዎች ክለባቸው በደረጃ ሰንጠረዡ ከቶትንሃም በላይ ሆኖ ሲያጠናቅቅ የሚያከብሩት በዓል “St Totteringham’s Day” በግርድፉ ”የቶትንሃም የውርደት ቀን” እንደማለት ሲሆን ይህም ሌላኛው የመበሻሸቂያ ጉዳይ ነው።

በየዓመቱ ቶትንሃም አርሰናልን ማነጻጸር የማይችልበት ደረጃ ላይ ሲደርስ (ለምሳሌ አርሰናል 70 ነጥብ፣ ቶትንሃም ደግሞ በቀሩት ጨዋታዎች ቢበዛ 68 ነጥብ ብቻ ይዞ የሚያጠናቅቅ ከሆነ) ደጋፊዎቹ “ዛሬ የቅዱስ ቶተሪንግሃም ቀን ነው!” ብለው በደስታ ያከብራሉ።

በተለይም አርሰናል በአሰልጣኝ አርሴን ቬንገር ስር ለ22 ዓመታት ያህል በደረጃ ሰንጠረዡ ሁልጊዜ ከቶትንሃም በላይ ሆኖ ባጠናቀቀባቸው ዓመታት ይህ ፌስቲቫል በትልቁ የመበሻሸቂያ በዓል ተደርጎ ይወሰዳል።

ይህ ባላንጣነት ዛሬም ድረስ በስታዲየም ውስጥ ካለ ጩኸት ባለፈ በቤተሰብ ፣ በጓደኛ እና በስራ ባልደረቦች መካከል የሚንጸባረቅ ጥልቅ ስሜት ነው።

በቶለሳ መብራቴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review