AMN- የካቲት 19/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ቤተ እምነቶች ይበልጥ ጎልተው እንዲታዩና ሳቢ እንዲሆኑ ማድረጉን ምዕመናን ገለጹ።
ኤ. ኤም. ኤን ቅኝት ባደረገባቸው በአፍንጮ በር አካባቢ የሚገኘው የአል-አቅሷ መስጊድ እና በቦሌ የሚገኘው የቦሌ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን በኮሪደር ልማቱ ውብ ገጽታን ከተላበሱት መሃል ይጠቀሳሉ፡፡
አል-አቅሷ መስጊድ ያገኘናቸው የእስልምና እምነት ተከታይ ሼህ አብደላ ሀሰን፣ መስጊዱ ያለበት ዙሪያ ከአራቱ ማዕዘን የሚወጣ ቆሻሻ መጥቶ ይደፋበት እንደነበር ነው የሚያስታውሱት፡፡
የክርስትና እምነት ተከታዩ ጥላሁን ወልዴ በቦሌ መድኃኔዓለም ቅጥር አካባቢ ለእይታ ሳቢ ያልሆኑ ነገሮች እንደነበሩና ሽታም ያስቸግር እንደነበር ገልጸዋል፡፡
አቶ መሐመድ ሰኢድም በአል አቅሷ መስጊድ ዙሪያ ይደፋ የነበረው ቆሻሻ ፀሐይ በሚሆንበት ጊዜ ሽታ ስለነበረው ኡዱ ለማድረግም ይቸገሩ እንነበር ነው የሚገልጹት፡፡
አሁን ላይ በአፍንጮ በር የሚገኘው የአል-አቅሷ መስጊድም ሆነ የቦሌ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አካባቢዎች በኮሪደር ልማትና በወንዝ ዳር ልማቱ ሙሉ በሙሉ ተቀይረው ሳቢና ንፁህ ሆነዋል፡፡

አሁን አል-አቅሷ መስጊድ እንደምታዩት ኮሪደር ልማቱ አሳምሮት ፓርኪንግም ሁሉ ነገር የተሟላ ሆኗል የሚሉት ሼህ አብደላ ሀሰን፣ በጥሩ ሁኔታ ኢባዳ እናካሂድበታለን ብለዋል፡፡
የቦሌ ቤተክርስቲያንም ቅጥር ዙሪያም በጣም የተዋበ፣ መሆኑንና በብርሃን ፈክቶ ማታ ማታ ላይ እንደውም እይታው በጣም የተለየ ገጽታ እዳለው ጥላሁን ወልዴ ተናግረዋል፡፡
የወንዝ ዳር ልማቱ መሰራት አል አቅሷ መስጊድን ጽዱ እንዲሆን ማድረጉን አቶ መሐመድ ሰኢድም በደስታ ነው የሚገልጹት፡፡
ቀደም ብሎ ለእይታም ሆነ ለሽታ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮች እንደነበሩ የሚጠቅሱት አቶ ሰይፈ ሚካኤል፣ የቦሌ መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን አሁን ላይ ምቹና ውብ መሆኑን የእግረኛ መንገድ መስፋቱን፣ በቅጥሩ ዙሪያ ቆሞ ስብከት ለመስማት ሳቢ መሆኑን ዘርዝረዋል፡፡
ሃጂ ሰኢድ ክብረት የወንዙ ዳር ያ ሁሉ ቆሻሻ ተነስቶ መዝናኛ፣ መናፈሻ፣ እንደዚህ መስገጃ መሆኑ ለእኔ ትልቅ ተአምር ነው ብለዋል፡፡
አማንያኑ እንደሚገልጹት፣ የቤተ እምነቶች አካባቢ ውብ፣ ንፁህና ምቹ ከመሆኑ ባለፈ አማኙ ይበልጥ ወደ ቤተ እምነቶች እንዲቀርብና ረዘም ያለ ቆይታ እንዲያደርግም ይጋብዛል።
በታደሰ ሽፈራው