አዲስ አበባን እንደ ስሟ ዉብ አበባ ለማድረግ በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች መዲናዋ የአፍሪካ የዲፕሎማሲና የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል ለመሆን በቅታለች

You are currently viewing አዲስ አበባን እንደ ስሟ ዉብ አበባ ለማድረግ በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች መዲናዋ የአፍሪካ የዲፕሎማሲና የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል ለመሆን በቅታለች

AMN የካቲት 19/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ ለረጅም አመታት የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም ዋና ከተማ ሆና አገልግላለች፤ በማገልገል ላይም ትገኛለች፡፡

አዲስ አበባ ከ150 በላይ ኤምባሲዎች ያሉባት፤ እንደ አፍሪካ ሕብረትና የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዓይነት ታላላቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫም ናት፡፡

መዲናዋ ዘመናት የተሻገረ የከተማ ታሪክ፤ ማራኪ ስያሜ እና ለመልማት የሚያመች ተፈጥሮአዊ አቀማመጥ እና ጸጋዎች ቢኖሯትም የታሪኳን፤ የስሟን እና ለመልማት ያላትን ዕድል ያህል ሳታድግ እና ሳትጠቀምበት ኖራለች፡፡

ለዘመናት ያልተፈቱ የመሰረተ ልማት እና የማህበራዊ አገልግሎቶች ችግር ፤ የዘመናዊነትና የተደራሽነት ፈተናዎች መዲናዋ በሚፈለገዉ መጠን እንዳትለማ ፈተና ሆነዉባት ቆይተዋል፡፡

አዲስ አበባ በፍጥነት እያደገ የመጣውን የነዋሪዎቿን ፍላጎት ከማሟላት፤ ለኑሮ እና ለተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴች ምቹ ከመሆን ረገድም በርካታ ዉሱንነቶች ገጥመዋታል፡፡

ከለዉጡ ወዲህ ትናንት የነበሩ ዉሱንነቶችን ከመፍታት፤ ዓለም የደረሰበትን የከተማ ደረጃ ከማላበስና ለነገዉ ትዉልድ የምትመች አዳጊ ከተማ ከመፍጠር ረገድ በርካታ የልማት ስራዎች በጥቂት ዓመታት ዉስጥ ተከናዉነዋል፡፡

የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎችን ጨምሮ በመዲናዋ የተከናወኑ ሌሎች ዘርፈ ብዙ የልማት እና ሰው ተኮር ስራዎች አዲስ አበባን እንደ ስሟ አበበና የኢትዮጵያ ብልጽግና ማሳያ ከተማ አድርገዋታል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከልማቱ ባሻገር በርካታ አስተዳደራዊ፤ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመቅረፍ በአፍሪካ እና በአለም አቀፍ ደረጃ ተሞኮሮ የሚቀመርባቸዉን ዉጤቶች አስመዝግቧል፡፡

በተከናወኑት ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችም በህብረብሄራዊ አንድነት የደመቀችዉ አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ ምቹ፤ የአፍሪካ የዲፕሎማሲና የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል ለመሆን በቅታለች፡፡

አዲስ አበባ ለሌሎች ከተሞች ምሳሌ የምትሆን ሥሉጥ ከተማ፤ በዲጂታል ዘመን ቴክኖሎጂን የዋጀች፤ የታደሰች እና እንደ አዲስ እየለማች የምትገኝ መዲና ሆናለች፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review