ጋብቻን ለመመዝገብ ስልጠና መውሰድ አስገዳጅ አይደለም- ኤጀንሲው

You are currently viewing ጋብቻን ለመመዝገብ ስልጠና መውሰድ አስገዳጅ አይደለም- ኤጀንሲው

AMN- የካቲት 20/2018 ዓ.ም

በአንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች “ስልጠና ካልተወሰደ ጋብቻ አይመዘገብም” ተብሎ የሚናፈሰው መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ገለጸ።

ኤጀንሲው፤ ጥንዶች ለጋብቻ ምዝገባ በሚመጡበት ወቅት ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ የሕግና የማኅበራዊ ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጥጋቡ ሹመይ ለኤ አም ኤን እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት እየተሰጠ ያለው አገልግሎት አጭር የግንዛቤ ማስጨበጫ እንጂ፣ ጋብቻን ለመመዝገብ እንደ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠ አስገዳጅ ስልጠና አለመሆኑን አብራርተዋል።

ተጋቢዎች ወደ ምዝገባ ማዕከላት በሚመጡበት ወቅት በባለሙያዎች አማካኝነት ለጥቂት ደቂቃዎች የሚቆይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እንደሚሰጣቸውም አንስተዋል።

ይህ የምክር አገልግሎት በዋናነት ስለ አጠቃላይ የጋብቻ ሥርዓት ግንዛቤ ለመፍጠርና የጋብቻ ሥርዓቱ ከንብረት ወይም ከሀብት ጋር ያለውን የሕግ ቁርኝት ለማስረዳት ታስቦ የሚከናወን መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህ አሰራር ተጋቢዎች በጋራ ሕይወታቸው ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ የሕግ ክፍተቶችን አስቀድመው እንዲረዱ ለማድረግ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ኤጀንሲው ይህንን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በገፅ ለገፅ ውይይቶችና በተለያዩ የመረጃ ማሰራጫ ዘዴዎች ለኅብረተሰቡ እያደረሰም ይገኛል።

አቶ ጥጋቡ አክለውም፤ እስካሁን ባለው አሠራር ጋብቻን ለመመዝገብ ስልጠና መውሰድ በሕግም ሆነ በመመሪያ ግዴታ አለመሆኑን አረጋግጠዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review