ከወረቀት ጋጋታ ወደ ዲጂታል ቅልጥፍና፦ የአዘርባጃን አስደናቂ የመንግሥት አገልግሎት ሽግግር

You are currently viewing ከወረቀት ጋጋታ ወደ ዲጂታል ቅልጥፍና፦ የአዘርባጃን አስደናቂ የመንግሥት አገልግሎት ሽግግር

AMN – የካቲት 20/2018 ዓ.ም

አዘርባጃን በአንድ ወቅት በቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረድና በወረቀት ሥራ ትታወቅ የነበረች ቢሆንም፣ ዛሬ ግን በቴክኖሎጂ የታገዘ የመንግሥት አገልግሎት በመዘርጋት የዓለምን ትኩረት መሳብ ችላለች። ሀገሪቱ ያስመዘገበችው አስደናቂ ሽግግር በዲጂታል መንግሥት ግንባታ ከዓለም ቀዳሚ ተርታ እንድትሰለፍ አስችሏታል።

ይህ የታሪክ ምዕራፍ የተቀየረው፣ ሀገሪቱ ዜጎቿን ከቢሮክራሲ እንግልት ነፃ ያደረገ ሁሉንም አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል የማግኘት የፈጠራ መፍትሔ በማምጣቷ እንደሆነ ይነገራል።

በ2012 የተመሠረተው አሳን ኺዝመት ( ASAN Service) በአዘርባጃን ቋንቋ ‘ቀላል አገልግሎት’ የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን፣ ሀገሪቱ ለጀመረችው የመንግሥት አገልግሎት ሽግግርም እንደ ዋና ሞተር ተደርጎ ይወሰዳል።

አሳን ኺዝመት የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሲሆን ፓስፖርት፣ የመንጃ ፈቃድ፣ የልደት ምስክር ወረቀትና የንግድ ምዝገባን ጨምሮ ከ300 በላይ አገልግሎቶችን በአንድ ጣራ ስር ይሰጣል።

አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የታገዘና ግልጽ በመሆኑ በባለስልጣናትና በዜጎች መካከል የነበረውን ቀጥተኛ ንክኪ በመቀነስ ሙስናን በከፍተኛ ደረጃ መግታት መቻሉም ተረጋግጧል።

አገልግሎቱ ወደ ማዕከላቱ መምጣት ለማይችሉ ዜጎችም አልቀረም፡፡ በዘመናዊ አውቶቡሶችና ባቡሮች የተደራጁ ተንቀሳቃሽ የASAN ቢሮዎች አገልግሎቱን እስከ ራቅ ያሉ የገጠር መንደሮች ድረስ በመውሰድ የመንግሥትን አገልግሎት በዜጎች ደጃፍ ላይ አቅርበዋል።

የአዘርባጃን የዲጂታል አብዮት ሌላኛው ስኬት የዜጎችን መረጃ በዘመናዊ መልክ ማደራጀቱ ነው። እያንዳንዱ ዜጋ የዲጂታል መታወቂያ (Digital ID) እንዲኖረው በመደረጉ፣ ዜጎች በየትኛውም የዓለም ክፍል ሆነው የመንግሥት አገልግሎቶችን በኢንተርኔት አማካኝነት በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ መንገድ ከፍቷል።

የኤሌክትሮኒክስ ፊርማ (Asan Imza) አጠቃቀም በንግዱ ማኅበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት በማግኘቱ፣ ውሎችንና ግብይቶችን በሞባይል ስልክ ብቻ ማከናወን የተለመደ ሆኗል።

የአዘርባጃን የቴክኖሎጂ ሽግግር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አድናቆትን እያተረፈ ሲሆን፣ ለአብነትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ2015 አሳን የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ረገድ የላቀ ውጤት ላመጡ ተቋማት የሚሰጠውን ሽልማት አሸንፏል።

እንደ ሞንጎሊያ፣ አፍጋኒስታንና አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት የአዘርባጃንን ሞዴል ወደ አገራቸው ለመቅዳት ከባኩ ጋር ስምምነት መፈራረማቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

አዘርባጃን አሁን ላይ አገልግሎቶቿን ይበልጥ ለማሳለጥ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ላይ ኢንቨስት እያደረገች ትገኛለች።

ይህም የዜጎችን ጥያቄዎች በሮቦቶች (Chatbots) አማካኝነት ምላሽ መስጠትና የመረጃ ደህንነትን (Cybersecurity) ማጠናከርን ይጨምራል።

የአዘርባጃን ተሞክሮ እንደሚያሳየው፣ ቴክኖሎጂን ከጠንካራ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ጋር በማቀናጀት የመንግስትን አገልግሎት ማዘመንና የዜጎችን እምነት መገንባት እንደሚቻል ትልቅ ትምህርት የሚወሰድበት ስለመሆኑ ታምኖበታል።

ኢትዮጵያ እና አዘርባጃን በጂኦፖለቲካዊ አቀማመጥ፣ በታሪክ ሂደት እና በቅርብ ጊዜያት እያከናወኗቸው ባሉ የሪፎርም ሥራዎች በርካታ የሚያመሳስሏቸው ነጥቦች አሏቸው።

ሁለቱም ሀገራት ቢሮክራሲን ለመቀነስ እና ሙስናን ለመዋጋት ቴክኖሎጂን እንደ ዋና መፍትሔ ወስደዋል። አዘርባጃን በ”አሳን ኺዝመት” (ASAN Service) የመንግስት አገልግሎት እያሳለጠች ሲሆነ ኢትዮጵያም በመሶብ አንድ ማዕከል የመንግስት አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እያደረገች ትገኛለች፡፡

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review