የአዲስ አበባ የሰላም ተምሳሌትነት

You are currently viewing የአዲስ አበባ የሰላም ተምሳሌትነት

“ሰላምን አስተማማኝና ዘላቂ ለማድረግ ሕዝብን የሰላም ባለቤት ማድረግ ወሳኝ ነው”

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ

ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው። ከተሞችን ለሥራ፣ ለንግድና ቱሪዝም እንዲሁም ለኑሮ ተመራጭ ከሚያደርጓቸው ወሳኝ ጉዳዮች መካከል አንዱና ዋነኛው ሰላም ነው። ዜጎች በሰላም ወጥተው መግባት፣ ያለገደብ ተንቀሳቅሰው መሥራት የሚችሉበትን ሁኔታ የፈጠሩ፣ ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ የቻሉ፣ ዝቅተኛ የወንጀል ምጣኔ ያለባቸው ከተሞች ለኑሮ ተመራጭ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የአፍሪካውያን መናኸሪያ፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ፣ በዓለም ሦስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችውን አዲስ አበባን ሰላምና ጸጥታዋን ዘላቂ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። የተለያዩ የጸጥታ አካላትንና ሕብረተሰቡን በማሳተፍ እና የጸጥታ ሥራውን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የሚሠራው ሥራ ከተማዋን ሰላማዊና ደህንነቷ የተጠበቀ እንድትሆን አስችሏል። ይህ ተሞክሮ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ሊሰፋ እንደሚገባ በትላንትናው ዕለት በጀመረውና በዛሬው ዕለት በሚጠናቀቀው ሀገር አቀፍ የሰላምና ጸጥታ የጋራ ምክክር መድረክ ተገልጿል።

8ኛው ሀገር አቀፍ የሰላምና ጸጥታ ምክክር መድረክ “ሰላማዊ ፖለቲካ ለሀገራዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ በሰላም ሚኒስቴር እና በአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ በጋራ በመሆን በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ባለው የምክክር መድረክ ሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች፣ የፌዴራል ተቋማት እና ሌሎች የሰላምና ጸጥታ ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገች ባለበት ወቅት የተካሄደው የምክክር መድረኩ፤ የሕዝብ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነት መገለጫ የሆነው ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ አሳታፊና ተአማኒነት ያለው እንዲሆን ለማድረግ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫና በድህረ ምርጫ ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የሰላም ችግሮችን ለመፍታት ምክክር የሚደረግበት እንደሆነም ተገልጿል።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ በአዲስ አበባም ሆነ በመላ ሀገሪቱ ሰላምን ለማረጋገጥ ሕዝብን የሰላም ባለቤት ማድረግ ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል። ከንቲባዋ በይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት “ሰላምን አስተማማኝና ዘላቂ ለማድረግ ሕዝብን የሰላም ባለቤት ማድረግ ወሳኝ ነው። በዚህ ረገድ መዲናችን አዲስ አበባ ስኬታማ ተሞክሮ ያላት በመሆኑ፣ ለሌሎችም ሰፊ ልምድ ታካፍላለች” ብለዋል።

“የዘላቂ ሰላም መስፈን ለልማት ሥራዎቻችን ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፤ የሁሉን አቀፍ ልማት መረጋገጥ ደግሞ በምላሹ አስተማማኝ ሰላምን ያሰፍናል” ያሉት ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ አዲስ አበባ በሁለንተናዊ መልኩ ሕዝብን በማሳተፍ በምትሠራው ሥራ የሕዝብን ባለቤትነት መፍጠር እንደቻለች ተናግረዋል።

የሰላም ሚኒስትር አቶ መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው አዲስ አበባ በልማትም ሆነ ሰላምና ጸጥታን በማስጠበቅ አርዓያ መሆኗን ተናግረዋል። በከተማዋ የሰላምና ጸጥታን የማረጋገጥ ሥራ ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖረው የተሠራው ሥራ ከተማዋን ሰላምና ደህንነቷ የተረጋገጠ እንዲሆን በማድረግ ውጤታማ መሆኑንና ይህንንም መልካም ተሞክሮ ሌሎች ክልሎችና ከተሞች ሊወስዱት ይገባል ብለዋል። በከተማዋ ከሚሠሩ የልማት ሥራዎች ጎን ለጎን በቴክኖሎጂ ታግዞ እየተከናወነ ያለው ሰላምን የማስፈንና ወንጀልን የመከላከል ሥራ ውጤታማ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ እንዲሁ በአዲስ አበባ በጸጥታ አካላትና በሕብረተሰቡ መካከል በቅንጅት በተሠራው ሥራ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ተችሏል። በተለይ ሕብረተሰቡ በሰላም ሠራዊት በመሳተፍ የአካባቢውና የከተማዋ ሰላምና ጸጥታ እንዲረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ደረቅ ወንጀሎችን፣ ሰላምን ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ሰርጎ ገቦችንና ጸጉረ ልውጦችን በመከላከልም ውጤታማ መሆን ተችሏል። በተጨማሪ ከአጎራባች ክልሎች በተለይ ከሸገር ከተማ አስተዳደር ጋር በቅንጅት በመሥራት የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ አስተማማኝ ማድረግ ተችሏል። ባለፉት ወራት ሚሊዮኖች በአደባባይ ወጥተው ያለምንም የሰላምና ጸጥታ ችግር በዓላትን ማክበር መቻላቸው ለዚህ ማሳያ እንደሆነ አንስተዋል።

ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ሁሉን አሳታፊ እና የሀገረ መንግሥት ግንባታውን የሚያጸና እንዲሆን መንግሥት በቁርጠኝነት እየሠራ እንደሚገኝ አንስተው፣ ምርጫ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ለመመሥረትና ዘላቂ የሆነ ሰላምና መረጋጋት የሚያመጣ በመሆኑ ለስኬታማነቱ ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ለዘመናት የግጭት ምክንያት የሆኑ ልዩነቶችን ከምንጫቸው ለማድረቅ፣ የሕዝብን የሰላም እሴቶች ለማዳበር፣ በብሔራዊ ምክክር በመፍታት አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሁሉም እገዛ አስፈላጊ እንደሆነም አክለዋል።

በመድረኩ እንደተገለጸው አዲስ አበባን ልክ እንደ ስሟ ውብና አዲስ፣ ለነዋሪዎችና ጎብኚዎች የምትመች ከተማ ለማድረግ በተሠራው ሥራ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች እየጨመሩ መጥተዋል። በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ብቻ 150 አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች በአዲስ አበባ በሰላም ማከናወን ተችሏል። በዚህም የሀገርን መልካም ገጽታ መገንባት እንደተቻለ ተገልጿል። በከተማዋ የጸጥታ ሥጋቶችን አስቀድሞ አጥንቶ እርምጃ በመውሰድ፣ በኮሪደር ልማቱ ሰላምንና ጸጥታን፣ ወንጀልን ለመከላከል የሚረዱ ዘመናዊ የደህንነት ካሜራዎችን በመግጠም፣ ሕብረተሰቡን በማሳተፍ የተሠሩ ሥራዎች ሰላምና ደህንነቷ የተጠበቀ እንድትሆን በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review