የኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ጥቁምታ

You are currently viewing የኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ጥቁምታ

በመዲናችን አዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም መሰል መርሃ ግብር መቅረባቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ከተሰናዱ መካከልም የስዕል አውደ ርዕይ እና የመጽሐፍት ውይይት ይገኙበታል። ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጥቂቶቹን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡

መጻሕፍት

በደራሲ ሮማን ገብረመድህን በተጻፈው ዮዲታ ግለታሪክ መጽሐፍ ላይ ዛሬ ከ8፡00 ሰዓት ጀምሮ ውይይት ይካሄዳል፡፡ ውይይቱን ያሰናዳው ዛጎል የመጻሕፍት ባንክ ሲሆን የውይይቱ አዘጋጅና አቅራቢ ደግሞ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ነው።

ውይይቱ የሚካሄድበት ሥፍራ ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (FSS) አዳራሽ ሲሆን፣ ቀበና ካቶሊክ፣ ኪዳነምሕረት ቤተክርስቲያን አቅራቢያ፣ ወደ ሳንፎርድ ትምህርት ቤት በሚወስደው መንገድ፣ ባማ አዲስ ሕንፃ አጠገብ ይገኛል፡፡

በሌላ መረጃ አንጋፋው ደራሲ ሲሳይ ንጉሱ፣ ከረዥም ዓመታት ቆይታ በኋላ “ሳልሳዊ ልደት” የተሰኘ አዲስ የመጽሐፍ ስራውን ለንባብ ሊያበቃ መሆኑን ኤቨንት አዲስ ሚዲያ ዘግቧል። ደራሲው በተለይም በታዋቂው “ሰመመን” ልብ-ወለድ መጽሐፉ  በብዙዎች ዘንድ የሚታወስ ሲሆን፣ በተጨማሪም “የቅናት ዛር”፣ “ረቂቅ አሻራ” እና ሌሎች ተወዳጅ መጽሐፍትን ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል።

የጥበብና የሐሳብ ውይይት

“የቶሪኖው ግብዣና የሚጨሰው ጠረጴዛ” ላይ ውይይት ይደረጋል፡፡ ነገ የዓድዋ ድልን ምክንያት በማድረግ ከዓመት በፊት በጣሊያን ቶሪኖ በቀረበው “የሚጨሰው ጠረጴዛ” በተሰኘው የሥነ ጥበብ ሥራ ላይ ነው ውይይት የሚካሄደው፡፡ ይህን የሥነ ጥበብ  ስራ አዘጋጅቶ ያቀረበው እውቁ መምህር፣ ቀራጺና ሰዓሊ ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን ነው፡፡ በዚህ ዝግጅት ላይም የመነሻ ሐሳብ የሚያቀርበው ራሱ ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን ይሆናል፡፡  የጥበብና የሃሳብ ውይይቱ የሚጀምረው ከቀኑ 8:00 ሰዓት ላይ ሲሆን፣ ውይይቱ የሚደረግበት ቦታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት (ወመዘክር) መርስዔ ኃዘን ወልደ ቂርቆስ አዳራሽ ውስጥ ነው፡፡ ያሰናዳው ደግሞ  የዐውደ ፋጎስ የውይይት ክበብ ነው።    

 የስእል አውደ ርእይ

“አደይ አበባ” የስዕል አውደ ርዕይ በዛሬው ዕለት ለእይታ ይበቃል፡፡ በገብረ ክርስቶስ ደስታ ዘመናዊ የሥነ ጥበብ ማዕከል በይፋ የሚከፈተው ይህ አውደ ርዕይ፣ በተለያዩ ጊዜያት የተሳሉ ሥዕሎች ለጥበብ አፍቃሪያን የሚቀርቡበት ነው ተብሏል፡፡ በሰዓሊ ጀርማይ ሚካኤል ተዘጋጅቶ ለዕይታ የሚያቀርበው ይህ አውደ ርዕይ፤ ሰዓሊው በአለ የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት በነበረው ቆይታ ከሌሎች ከያኒያን፣ ተማሪዎችና የጥበብ አፍቃሪዎች ጋር በነበረው ማኅበራዊ መስተጋብር ያዳበራቸውን የፈጠራ ሥራዎች ያካተተ ነው ተብሏል። ከቀኑ 10፡00 ሰዓት የሚከፈተው ይህ መርሃ ግብር  እስከ መጋቢት 12 ቀን ድረስ ለጥበብ አፍቃሪያን ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ታውቋል።

በሌላ መረጃ 7 ሰዓሊያን የተሳተፉበት “ዓድዋ” የተሰኘ  የቡድን የስእል አውደ ርዕይ በእይታ ላይ ይገኛል፡፡  አውደ ርእዩን ያዘጋጁት አኑማ ሃይሉ፣ የሱቃል ተስፋዬ፣ ዮርዳኖስ ውቤ፣ እዮብ እሸቱ፣ ሱራፌል ከተማ፣ ዮዲት ወልደማርያም እና ዘካሪያስ ከተማ ናቸው፡፡ ፈንድቃ የባህል ማዕከል እና ሀያት ረጀንሲ ሆቴል በመተባበር ያዘጋጁት ይህ መርሃ ግብር እስከ የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም በእይታ ላይ ይቆያል፡፡

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review