ሰላም ልጆች! ሳምንቱ እንዴት አለፈ? ጥሩ ነው እንደምትሉ እርግጠኛ ነን። በዚህ ሳምንት ያዘጋጀንላችሁ ጽሑፍ የዓድዋን ድል የሚመለከት ነው፡፡ ለመሆኑ ስለዚህ ታሪክ ምን ያህል ታውቃላችሁ? ሀሳባችሁን ከቤተሰቦቻችሁ አልያም ከጓደኞቻችሁ ጋር ተለዋወጡ፡፡ ለመነሻ ይሆንላችሁ ዘንድ የሚከተለውን ጽሑፍ አዘጋጅተንላችኋል፡፡ ስለ ድሉ መረጃ የሚያጋሯችሁ እንግዳ ራሳቸውን በማስተዋወቅ ማብራሪያ ይሰጧችኋል፤ በተመስጦ እንድታነቡ ጋበዝናችሁ፡፡
ልጆች እንዴት ናችሁ? አባት አርበኛ መኮንን መሸሻ እባላለሁ፡፡ የዓድዋ ጦርነት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓመተ ምህረት በኢትዮጵያና በጣሊያን መካከል የተካሄደ ነው፡፡ ይህ ጦርነት በኢትዮጵያ አሸናፊነት ዓድዋ በሚባል አካባቢ ተጠናቋል፡፡ የዓድዋ ድል የተባለውም ለዚሁ ነው፡፡ ይህ ድል የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ትግል ውጤት ተደርጎም በዓለም ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያ ሊወራት የመጣውን ጣሊያንን እንድታሸንፍ የረዳት፣ በጦርነቱ ወቅት ኢትዮጵያውያን በብሔርና በኃይማኖት ሳይከፋፈሉ፣ ሴት ወንድ ሳይሉ በአንድነታቸው ቆመው መዋጋታቸው ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው በሀገራችን ጉዳይ ላይ በጋራ መቆም ለአሸናፊነት እንደሚያበቃ ነው፡፡
በዓድዋ ጦርነት ወቅት ጣሊያኖች ዘመናዊ መሣሪያ ታጥቀው ሊወጉን ቢመጡም፣ ኢትዮጵያውያን በአግባቡ ተደራጅተንና በአንድነት ቆመን ማሸነፍ ችለናል፡፡ በጦርነቱ ሴቶች በመዋጋትና በማዋጋት፣ ለራበውና ለጠማው ውሃና ምግብ በማቅረብ፣ የተመታውን ደሙን ባላቸው ጨርቅ እያሰሩ፣ እንዲሁም “በርታ ወደ ኋላ እንዳትል” እያሉ ሠራዊቱን በመደገፍ ታሪክ ሠርተዋል፡፡
ልጆች፤ በዓድዋ ጦርነት ወቅት 12 የጦር መሪዎች ነበሩ፡፡ እነዚህም መሪዎች፦ ፊታውራሪ ገበየሁ ገቦ ጉርሙ፣ ልዑል ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል ጉዲሳ፣ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ተሰማ ጎሹ፣ ንጉሥ ሚካኤል አሊ ሊበን፣ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ ሮባ፣ ራስ ወሌ ብጡል ኃይለ ማርያም፣ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ሁንዱል፣ ራስ አሉላ እንግዳ ቁቢ፣ ራስ መንገሻ ዮሐንስ ምርጫ፣ ዋግሹም ጓንጉል ብሩ ገብረ መድህን፣ ራስ አባተ ቧያለው ንጉሡ እና ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም ቢተርፉ ናቸው፡፡
ልጆች፤ ኢትዮጵያ የሰው ሀገር አትፈልግም፣ ራሷንም አታስደፍርም፤ ሲነኳትም አትወድም፡፡ በዚህም መሠረት በቅኝ ግዛት ያልተያዘች ሀገር ናት፡፡ እናንተም ለሀገራችሁ ትምህርታችሁን በርትታችሁ በመማር እና ከእናንተ የሚጠበቀውን በማድረግ ሀገራችሁን በዓለም ማስጠራት አለባችሁ፡፡
ልጆች፤ ስለ ድሉ የነገርኳችሁ በጥቂቱ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ፍቅር በአንድነት ወራሪውን የጣሊያን ጦር ድል ያደረጉበት፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁር ሕዝቦች ስለ ነፃነታቸውና ስለአንድነታቸው በጋራ መቆም እንዲችሉ ያስቻለው ድል 130ኛው ዓመት ዘንድሮ ይከበራል፡፡ መልካም በዓል ይሁንላችሁ፡፡
በፋንታነሽ ተፈራ