‘አይቻልም’ የሚለው ቃል በመዝገበ ቃላት ውስጥ ያለ ተራ ቃል ብቻ ሳይሆን፣ አንዳንድ ጊዜ ሰዎችና ሁኔታዎች በፊታችን ላይ የሚደቅኑት ግድግዳም ጭምር ሆኖ እናገኘዋለን። ይሁንና በታሪክ ውስጥ ይህንን ግድግዳ አምርረው ከናቁ ክስተቶች መካከል ሁለቱ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። አንደኛው ከአንድ ክፍለ ዘመን በፊት በዓድዋ ተራሮች ላይ በጀግኖች ኢትዮጵያውያን የተጻፈ የነፃነት ታሪክ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከስልሳ ዓመታት በኋላ በሮም አውራ ጎዳናዎች ላይ በጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ የተሠራው የጽናት ተአምር ነው።
ለአንድ አፍታ በምናብ ወደ ኋላ ወደ አስገራሚው የሮም ድል መለስ ብንል የምናየው ስሜት፣ ዓድዋ ላይ የነበረው ያ የማይበገር የነፃነት ወኔ በ1952 ዓ.ም በሻምበል አበበ ቢቂላ ልብ ውስጥ ዳግም ሲቀጣጠል ነው። አበበ በሮም አስፋልት ላይ በባዶ እግሩ ሲሮጥ፣ የሚረግጠው ድንጋዩንና ትኩሱን አስፋልት ብቻ አልነበረም፤ ‘ጥቁር ሕዝብ አይችልም’ የሚለውን የዓለምን የተሳሳተ አመለካከት ጭምር እንጂ።
የሮም ኦሎምፒክ ማራቶን ሊጀመር ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ፣ ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞችና ታዛቢዎች በአንድ ነገር ግራ ተጋብተው ነበር። አንድ ቀጭን ኢትዮጵያዊ ሯጭ፣ በዘመናዊው ስፖርት ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ያለምንም ጫማ በመነሻ መስመር ላይ ቆሟል። ያኔ ብዙዎች አበበ ቢቂላን እንደ አንድ ተራ ሯጭ ብቻ ሳይሆን፣ ጫማ የሌለው ምስኪን አፍሪካዊ አድርገው ነበር የቆጠሩት።
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ተራሮች ላይ ዓለምን ያስገረመ ታሪክ ሲሠሩ፣ ለአፍሪካውያንና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች “የማይቻል የለም” የሚል የድል ብርሃን ፈንጥቀው ነበር። ይህ የዓድዋ መንፈስ፣ ከ64 ዓመታት በኋላ በ1952 ዓ.ም በሌላ መልኩ በሮም አውራ ጎዳናዎች ላይ ዳግም ታየ። ይህ ክስተት የዓድዋ ድል በጦር መሣሪያ የተመዘገበ እንደሆነው ሁሉ፣ የሮም ድል ደግሞ ‘በላብና በጽናት’ የተመዘገበ ሁለተኛው የዓድዋ ድል ነበር። አበበ ቢቂላ ጫማ ባለመጫማቱ አልተሸማቀቀም፤ ይልቁንም “እግሬን የሚያቆስለኝ ጫማ እንጂ አስፋልቱ አይደለም” በሚል ኩራት፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በድል አደባባይ ላይ ከፍ አደረገ።
አበበ ቢቂላ ወደ ሮም ኦሎምፒክ ሲያቀና፣ አዳዲስ የሩጫ ጫማዎች እግሩን ስላቆሰሉት አንድ ከባድ ውሳኔ ወሰነ፤ በባዶ እግር መሮጥ፡፡ አስፋልቱ ይሞቃል፤ ድንጋዮቹ ይወጋሉ፤ ርቀቱ 42 ኪሎ ሜትር ነው። የሮምን አውራ ጎዳናዎች በባዶ እግሩ እየቀደደ፣ የፋሽስት ሞሶሊኒ ጦር ኢትዮጵያን ለመውረር የተነሳበትን የአክሱም ሐውልት አጠገብ አልፎ በመጀመሪያነት ሲገባ ዓለምን ያስገረመ ታሪክ ተሠራ።

የዓድዋ ድል ለመላው የጥቁር ሕዝቦች የድል ማሳያ እንደሆነ ሁሉ፣ የአትሌት አበበ ቢቂላ ድልም ለጥቁር አፍሪካውያን የመጀመሪያውን የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ በማምጣት በስፖርቱ ዓለም አዲስ ምዕራፍ ከፈተ። ዓድዋ ላይ ዘመናዊ መሣሪያ ሳይኖር በሀገር ፍቅር እንደተሸነፈ ሁሉ፣ አበበም ውድ ጫማ ሳይኖረው በጽናት አሸነፈ። በወቅቱ አትሌት አበበ ቢቂላ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው አስተያየት “ሁልጊዜም የምሮጠው ለድል ነው። ኢትዮጵያ ሁልጊዜም በጽናትና በድል አድራጊነት እንደምትኖር ለዓለም ማሳየት እፈልጋለሁ” ነበር ያለው፡፡
ታዋቂው የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት፣ የአበበን ድል ከአክሱም ሐውልት መመለስ ጥያቄ ጋር አያይዘውት ነበር። ፓንክረስት፣ ድሉ ለኢትዮጵያውያን የሰጠውን የሞራል ልዕልና ሲገልጹ፣ “አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ መሮጡ፣ ኢትዮጵያ ካሏት ሀብቶች ይልቅ በውስጣዊ ወኔና በሰው ኃይል ማንኛውንም ተግዳሮት ማሸነፍ እንደምትችል ለዓለም ያስመሰከረበት ክስተት ነበር” ብለዋል።
ብዙዎቹ አፍሪካውያን ምሁራን አበበን “የፓን-አፍሪካኒዝም አምባሳደር” ይሉታል። እ.ኤ.አ 1960 “የአፍሪካ ዓመት” ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን፣ በዚያው ዓመት አበበ የመጀመሪያውን ወርቅ ለአፍሪካ ማምጣቱ የተለያዩ ትርጉሞችን አሰጥቷል። በወቅቱ አውሮፓውያን “ጥቁር ሕዝብ ለረጅም ርቀት ሩጫ ብቃት የለውም” የሚለውን ሳይንሳዊ ግምት አበበ ውድቅ ማድረጉን ምሁራን በስፋት ጽፈውበታል። በሌላም በኩል ዓድዋ የጥቁር ሕዝብ የፖለቲካ ነፃነት ምልክት እንደሆነው ሁሉ፣ አበበ ቢቂላ ደግሞ የጥቁር ሕዝብ የአካልና የሥነ-ልቦና ብቃት ምልክት መሆኑን ያሰምሩበታል።
በዓድዋ ድል እና በአበበ ቢቂላ የሮም ድል መካከል ያለውን ተምሳሌታዊ ትስስር፣ የታሪክ አንድነት እና የስነ-ልቦና ጥንካሬ የመረመሩ በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎች አሉ። “Abebe Bikila: The Barefoot Runner and the Spirit of Adwa” የተሰኘው ጥናታዊ ጽሑፍ አበበ ቢቂላን እንደ “ሁለተኛው የዓድዋ ጀግና” ይስለዋል። ጥናቱ አበበ በሮም ኦሎምፒክ ያሸነፈው ሩጫ “የተገዥዎች በቀል” (Revenge of the Colonized) ተብሎ ሊጠራ እንደሚችል ይተነትናል። ጣሊያን ዓድዋ ላይ በጦር መሣሪያ የተሸነፈችውን ሽንፈት በሥልጣኔ ስም ልታክም በሞከረችበት መድረክ፣ አበበ በባዶ እግሩ መጥቶ ማሸነፉ የዓድዋን ድል በዲፕሎማሲና በስፖርት መድረክ ያደሰ ክስተት ስለመሆኑም በጥናቱ ላይ ሰፍሯል።
“Barefoot Runner: The Life of Marathon Champion Abebe Bikila” የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ እንግሊዛዊው ፖል ራምቦል በበኩላቸው፣ አበበን የሚስሉት እንደ ተራ አትሌት ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክና ኩራት መገለጫ አድርገው ነው።

አበበ ቢቂላ በሮም አውራ ጎዳናዎች ላይ በባዶ እግሩ ሲሮጥ፣ የተሸከመው የራሱን ሕልም ብቻ አልነበረም የሚሉት ፖል ራምቦል ይልቁንም ለዘመናት ሳይበገሩ የቆዩትን የአባቶቹን ጽናትና የዓድዋን የድል መንፈስ ጭምር ነው ይላሉ። አያይዘውም፣ ለእርሱ ሮም የውድድር ስፍራ ብቻ ሳትሆን፣ ኢትዮጵያውያን ለማንነታቸውና ለነፃነታቸው የሚከፍሉትን መሥዋዕትነት በስፖርታዊ ጨዋነት ለዓለም ዳግም የምታሳይበት መድረክ ነበረች። በዚያች ታሪካዊ ምሽት አበበ ያሸነፈው ሩጫውን ብቻ ሳይሆን፣ ‘ጥቁር ሕዝብ አይችልም’ የሚለውን የዓለምን ጥርጣሬ በደከመውና በቆሰለው እግሩ ረግጦ በማለፍ ጭምር ነበር ብለዋል፡፡
የዓድዋ ድል እና የአበበ ቢቂላ የሮም ድል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካውያን ‘የነፃነት’ እና ‘የችሎታ’ መገለጫ ተደርገውም ይወሰዳሉ። የዓድዋ ድል አውሮፓውያን አፍሪካን የመገዛት ዕጣ ፈንታ ያላት አድርገው ይስሏት የነበረውን ትረካ ሰባብሯል። ይህ ድል ለበርካታ የአፍሪካ ሀገራት የነፃነት ታጋዮች እንደ ብርሃን ሆኖ አገልግሏል። ብዙዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ነፃ ሲወጡ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ቀለሞች (አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ) ለባንዲራቸው መምረጣቸው የዓድዋ ድል ያስገኘው ተጨባጭ የፓን-አፍሪካኒዝም ማስረጃ ተደርጎም ሊወሰድ የሚችል ነው።
ከአበበ ድል በፊት፣ ረጅም ርቀት ሩጫ ለአውሮፓውያንና ለአሜሪካውያን ብቻ የተተወ ይመስል ነበር። የአበበ ድል በመላው አፍሪካ (በተለይ በምስራቅ አፍሪካ እንደ ኬንያ እና ታንዛኒያ) ለሚገኙ አትሌቶች መንገድ ከፋች ሆኗል። ዛሬ ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድሮች በአፍሪካውያን ቁጥጥር ስር መውደቃቸው፣ መነሻው የዓድዋ መንፈስ የወለደው የአበበ ቢቂላ ‘የይቻላል’ ጽናት ስለመሆኑም እሙን ነው።
አበበ ቢቂላ በሮም ኦሎምፒክ ሲያሸንፍ 17 የአፍሪካ ሀገራት ነፃነታቸውን ያገኙበት “የአፍሪካ ዓመት” ነበር። ዓድዋ አፍሪካውያን በጦር ሜዳ “እንችላለን” እንዲሉ እንዳደረጋቸው ሁሉ፣ አበበ ደግሞ ሰላማዊ በሆነው የዓለም ስፖርት መድረክ አፍሪካውያን ከነጭ ዘር እኩል አልፎም የተሻለ ብቃት እንዳላቸው በተግባር አሳይቷል።
የዓድዋ ድል የነፃነታችን መሠረት እንደሆነው ሁሉ፣ የአበበ ቢቂላ የሮም ድልም የኢትዮጵያውያን የጽናትና የ“ይቻላል” መንፈስ ማሳያ ሆኖ ለዘላለም ይኖራል። ዛሬም እንደ ሀገር የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ለማለፍ፣ ያንን ጥንካሬና የማይበገር ማንነት ዳግም ማንቃት ይጠበቅብናል። እንደዚሁም ዛሬ ስለ ዓድዋ ሲወራ ስለ ጦርነት ብቻ አይደለም የሚወራው፤ ዛሬ ስለ አበበ ቢቂላም ሲወራ ስለ ሩጫ ብቻ አይደለም የሚወራው። ይልቁንስ ዛሬ ላይ የሚወራው ማንኛውንም ተግዳሮት “ይቻላል” ብሎ ስለሚጋፈጠው ያ ኢትዮጵያዊ የጥንካሬ መንፈስ እንጂ።
በሳህሉ ብርሃኑ