ኢትዮጵያ በምታካሂደው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ሕዝቡ ንቁና ፍትሃዊ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሚዲያዎች ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ተገለጸ

You are currently viewing ኢትዮጵያ በምታካሂደው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ሕዝቡ ንቁና ፍትሃዊ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሚዲያዎች ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ተገለጸ
  • Post category:ፖለቲካ

AMN የካቲት 21/2018

ኢትዮጵያ በምታካሂደው 7ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ሂደት ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ሕዝቡ ንቁና ፍትሃዊ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሚዲያዎች ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ነዋይ ገለጹ።

አቶ ተስፋዬ ይህንን የገለጹት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር በመተባበር “የምርጫ ሂደትና የሚዲያ ሚና” በሚል መሪ ቃል ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ ነው።

በመድረኩ ላይ የብልጽግና ፓርቲ ተወካዮችን ጨምሮ በአዲስ አበባ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ የበርካታ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ተገኝተዋል።

ምርጫ ጠንካራ የዲሞክራሲ ስርዓት ለመገንባትና ለዜጎች እኩል ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል መንገድ መሆኑን የገለጹት አቶ ተስፋዬ፤ የምርጫ ሂደቱ ሁሉንም ያሳተፈ፣ ፍትሃዊና ሰላማዊ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ሚዲያዎች ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ነዋሪ ድምፅ በመሆን እያገለገለ የሚገኘው አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በከተማ ደረጃ ለሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎችና ለግል ተወዳዳሪዎች አጀንዳዎቻቸውንና የምርጫ ፕሮግራሞቻቸውን ለሕዝብ የሚያስተዋውቁበትን እኩል ዕድል በመስጠት የሚጠበቅበትን ሚና መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል።

በተለይም በምርጫው የሚሳተፉ ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዝግጅቶቻቸውና በሚወዳደሩባቸው አጀንዳዎች ላይ የሃሳብ ክርክር እንዲያደርጉ አመቺ ሁኔታዎችን በመፍጠር አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በማህበረሰቡ መካከል ግጭት ሊቀሰቅሱና ሰላምን ሊያውኩ የሚችሉ ሃሳቦችና መልዕክቶች እንዳይሰራጩ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸውም ተገልጿል።

በተለይም የሕዝብን ስሜት በአጭር ጊዜ ውስጥ በማነሳሳት ወደማይፈለግ አቅጣጫ ሊወስዱ የሚችሉ ጉዳዮችን ከማሰራጨት ፓርቲዎች ራሳቸውን መቆጠብ እንዳለባቸውና ለዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ምርጫ መስራት አስፈላጊ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታዉቋል፡፡

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለዲሞክራሲያዊና ግልጽ ምርጫ የሚያወጣቸውን ህጎችና መመሪያዎች ተፈጻሚ ማድረግ በምርጫው የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግዴታ መሆኑም ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ ውጤታማና ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጠንካራ መሰረት የሚጥል ምርጫ እንድታካሂድ፤ ሚዲያዎች የምርጫ ቦርድ ያወጣውን የሥነ-ምግባር ደንብ በመከተል የምርጫ መረጃዎችን ለሕዝቡ በግልጽነት ተደራሽ ማድረግ እንዳለባቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ከምርጫው በፊት ባሉ ስራዎች ላይ በስፋት መስራት እንዳለበት መልዕክት ተላልፏል።

በካስዬ ማንጉዳ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review