የኢትዮጵያና የአዘርባጃን ግንኙነት ከአገልግሎት ዘመናዊነት እስከ ስትራቴጂካዊ አጋርነት አድጓል -ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

You are currently viewing የኢትዮጵያና የአዘርባጃን ግንኙነት ከአገልግሎት ዘመናዊነት እስከ ስትራቴጂካዊ አጋርነት አድጓል -ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

AMN – የካቲት 22/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያና አዘርባጃን ግንኙነት ከአገልግሎት ዘመናዊነት እስከ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማደጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዘርባጃን የነበራቸውን ጉብኝት አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ እና በአዘርባጃን መካከል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ እንደገለጹት የሁለቱ ሀገራት ትብብር ከዲጂታል መንግስታዊ አገልግሎት ባለፈ በኢኮኖሚና በኢንቨስትመንት ዘርፎች ይበልጥ እየሰፋ መጥቷል።

በመሪዎች ደረጃ የተደረገው ጉብኝት ለግንኙነቱ መጠናከር ትልቅ መሰረት የጣለ ሲሆን፣በአዘርባጃን ተሞክሮ ተቀርጾ እና በኢትዮጵያ ስራ የጀመረው የመሶብ የመንግስታዊ አገልግሎት ማዕከል ውጤታማ የትብብር ተምሳሌት መደረጉንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያና የአዘርባጃን ግንኙነት ከኢንቨስትመንትና ከንግድ ባለፈ በቱሪዝም፣ በአቪዬሽን እና በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ አዳዲስ ስምምነቶች መፈረማቸው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከአገልግሎት ዘመናዊነት እስከ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማደጉን ያመላክታል ብለዋል፡፡

አዘርባጃንና ሌሎች አዳጊ ሀገራት ኢትዮጵያን ወደ አፍሪካ ገበያ ለመግባት እንደ ቀዳሚ ምርጫ በር እየመረጧት ይገኛሉ ያሉት ሚኒስትሩ፣ ለዚህም ዋና ዋና ምክንያቶችም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆኗ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰፊ የአህጉራዊ ሽፋንና ተፅዕኖ ፈጣሪ በመሆኑ፣ ስትራቴጂካዊ የጂኦግራፊ አቀማመጥ እና የህዝብ ብዛት ያላት ሀገር በመሆኗ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ባለው ተለዋዋጭ የዓለም ሁኔታ፣ ካፒታልና ቴክኖሎጂ ካላቸው ታላላቅ ሀገራት በተጨማሪ፣ ባለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት ፈጣን እድገት ካስመዘገቡና ተቀራራቢ ተሞክሮ ካላቸው አዳጊ ሀገራት ጋር ግንኙነቷን ለማጠናከር ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች እንደምትገኝም ተናግረዋል፡፡

አዘርባጃንም የእይታ አድማሷን በማስፋት ወደ አፍሪካ ለመሰማራት ያላትን ፍላጎት በተግባር እያሳየች ሲሆን፣ ለዚህ ደግሞ ተመራጯና ቀዳሚዋ ሀገር ኢትዮጵያ መሆኗን ተረድታለች ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)።

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review