AMN- የካቲት 22/2018 ዓ.ም
በ28ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ተጠባቂው ጨዋታ በአርሰናል እና ቼልሲ መካከል በኤምሬትስ ይደረጋል።
የሊጉ መሪ አርሰናል ከተከታዩ ማንችስተር ሲቲ ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ለማስፋት ድሉ ያስፈልገዋል።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ ከብሬንትፎርድ እና ዎልቭስ ጋር የጣላቸውን ነጥቦች የሚያካክስ ድል ቶተንሃም ሆትስፐርስን 4ለ1 በማሸነፍ አግኝቷል።
የሚካኤል አርቴታው ቡድን ከ22 ዓመታት በኋላ የሊግ ዋንጫውን ለማሳካት በቀሪ ጨዋታዎቹ ተመሳሳይ ድል ማስመዝገብ ይጠበቅበታል።
ቼልሲ ወጥነት በጎደለው ጉዞው ቀጥሏል። የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ኢንዞ ማሬስካን አሰናብቶ ሊያም ሮሲኒዮር ማምጣቱ የጎላ ለውጥ አልፈጠረለትም። በተለይ በሜዳው ስታምፎርድ ብሪጅ ከሊድስ ዩናይትድ እና በርንሌይ ጋር አቻ መለያየቱ ደጋፊዎችን አላስደሰተም።
በቀጣይ ፈታኝ ጨዋታዎች ያሉበት ቼልሲ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎ የሚያገኝበትን ደረጃ ይዞ ለማጠናቀቅ ተከታታይ ድል ያስፈልገዋል።
ቼልሲ በውድድር ዓመቱ አርሰናልን ሦስት ጊዜ ገጥሞ አንዱንም አላሸነፈም። በካራባኦ ካፕ ግማሽ ፍፃሜ የደርሶ መልስ ጨዋታዎችን አርሰናል ሲያሸንፍ ፣ በሊጉ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታቸው ደግሞ 1ለ1 መለያየታቸው ይታወሳል።
ሁለቱ ክለቦች በፕሪምየር ሊጉ ታሪክ አይረሴ ፍልሚያዎችን አስመልክተዋል። በቅርብ ዓመታት የሀይል ሚዛኑ ወደ አርሰናል አድልቷል።
ሚካኤል አርቴታ በ2019 አርሰናልን ከተረከበ በኋላ ሁለቱ ክለቦች በሁሉም ውድድር 16 ጊዜ ተገናኝተው ቼልሲ ማሸነፍ የቻለው ሁለቱን ብቻ ነው። አርሰናል 10 ሲያሸንፍ አራቱን አቻ ተለያይተዋል።
ዛሬስ? በዋና ዳኛ ዳረን ኢንግላንድ ፊሽካ ምሽት 1:30 የሚጀምረው ጨዋታ ምላሽ ይሰጠናል።
ዛሬ በሚደረጉ ሌሎች ጨዋታዎች ማንችስተር ዩናይትድ በኦልድትራፎርድ ክሪስታል ፓላስን ያስተናግዳል።
በማይክል ካሪክ እየተመራ ትልቅ ለውጥ ላይ የሚገኘው ዩናይትድ ድል ከቀናው አስቶንቪላን በግብ ክፍያ በልጦ ወደ 3ኛ ደረጃ ከፍ ይላል። ጨዋታው 11 ሰዓት ላይ ይጀምራል።
ፉልሃም ከ ቶተንሃም ሆትስፐርስ እንዲሁም ብራይተን ከ ኖቲንግሃም ፎረስት በተመሳሳይ 11 ሰዓት ላይ የሚጀምሩ ሌሎች ጨዋታዎች ናቸው።
በሸዋንግዛው ግርማ