AMN- የካቲት 22/2018 ዓ.ም
በአሁኑ ወቅት በዓለማችንም ሆነ በሀገራችን በርካታ ሰዎች የአፍንጫ አለርጂ ሰለባ እየሆኑ ይገኛሉ።
ብዙ ጊዜ ከሳይነስ ህመም ጋር የሚቀላቀለው ይህ የጤና እክል፣ በተለይ ወቅትን ጠብቆ የሚከሰት ወይም በአካባቢ ብክለት ምክንያት የሚቀሰቀስ መሆኑን በየካቲት 12 ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ሀኪም ዶ/ር ሰላም ቦጋለ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡
ይህ የጤና ችግር የሚከሰተው የሰውነት በሽታ የመከላከል ሥርዓት በአየር ውስጥ ያሉ ለጤና ጎጂ ያልሆኑ ነገሮችን እንደ ባዕድ በመቁጠር ከልክ ያለፈ ምላሽ በሚሰጥበት ወቅት መሆኑን ዶ/ር ሰላም አብራርተዋል።

በዚህ ሂደት በሰውነት ውስጥ ሂስታሚን የተባለ ኬሚካል ወደ ደም ውስጥ ስለሚለቅ በአፍንጫ ውስጥ ያሉ ስስ ብልቶች እንዲቆጡና እንዲያብጡ ያደርጋል።
ሁኔታው በአብዛኛው የሚቀሰቀሰው ከአበባ ብናኝ፣ በምንጣፍና በአሮጌ እቃዎች ውስጥ በሚገኝ አቧራ፣ እንዲሁም በቤት እንስሳት ፀጉርና በተለያዩ ኃይለኛ ሽታዎች አማካኝነት እንደሆነም ዶ/ር ሰላም አስረድተዋል።
የአለርጂው ተጠቂዎች እንደየሁኔታው የተለያዩ ምልክቶች የሚያስተዋልባቸው ሲሆን፣ በተከታታይ ማስነጠስ፣ የአፍንጫ ማሳከክ እና ውሃ የመሰለ ፈሳሽ ከአፍንጫ መፍሰስ በዋናነት ይጠቀሳሉ።
በተጨማሪም የአፍንጫ መታፈንና ለመተንፈስ መቸገር፣ የዓይን መቅላት፣ ማሳከክና እንባ መፍሰስ ሊከሰት የሚችል ሲሆን፣ እነዚህ ምልክቶች በተለይ ጠዋት ጠዋት ይበልጥ ይበረታሉ።

ዶ/ር ሰላም እንደሚመክሩት፣ የአፍንጫ አለርጂን ለመቆጣጠር ቀዳሚውና ውጤታማው መንገድ ቀስቃሽ ሁኔታዎችን ለይቶ ማወቅና ከእነርሱ መራቅ ነው።
መኖሪያ ቤትን ከአቧራ ነፃ ማድረግ፣ አቧራማ በሆኑ ቦታዎች ወይም የአበባ ብናኝ በሚበዛባቸው ወቅቶች አፍና አፍንጫ በማስክ መሸፈን ተገቢ መሆኑንም ይገልፃሉ።
አፍንጫን በጨው ውሃ መታጠብ አቧራንና አለርጂ ቀስቃሾችን ከአፍንጫ ውስጥ ለማፅዳት ትልቅ እገዛ የሚያደርግ ሲሆን፣ ምልክቶቹ ሲበረቱ ደግሞ እንደ አንቲ-ሂስታሚን ያሉ መድኃኒቶችን እና የአፍንጫ ስፕሬዮችን በሕክምና ባለሙያ ትዕዛዝ በመውሰድም ከበሽታው መፈወስ እንደሚቻል ዶ/ር ሰላም ቦጋለ አብራርተዋል፡፡
በበረከት ጌታቸው