AMN – የካቲት 22/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከኢትዮጲያ ፖሊስ ዩንቨርስቲ ጋር በመተባበር ከ1ኛ እስከ 3ኛ ዙር በልዩ ልዩ የአደጋ መከላከልና ምላሽ አሰጣጥ ዘርፎች ሲያሰለጥናቸው የቆዩ የፓራ ሚሊተሪ ሰልጣኞች አሰመረቋል።
በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ፣ አዲስ አበባ ከተማ ለነዋሪዎቿ ብቻ ሳትሆን የኢትዮጵያዊያን ብሎም የአፍሪካዊያን መዲና መሆኗን አንስተው ከተማዋን ከአደጋ ስጋት ነፃ ማድረግ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢንጂነር ወንድሙ አክለውም የመዲናዋን ነዋሪዎች ህይወትና ንብረት ከአደጋ ለመከላከል የአደጋ መከላከል፣ መቆጣጠር፣ እና ምላሽ መስጠት ላይ ዘመኑን የሚዋጅ ዲጅታል ስርአትን ከመዘርጋትም ባለፈ በጥበብ የሚመራ ባለሙያን ማፍራት ተገቢ ነው ብለዋል።
የእሳትና አደጋ ስጋት ስራዎች ሙያዊ ብቻ ሳይሆኑ ሰብአዊ ተግባር የሚገለጥባቸው መሆኑን ያነሱት ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ፣ ተመራቂዎች የአዲስ አበባን ሰላምና ደህንነት በላቀ ደረጃ በመጠበቅ የነዋሪዎችን ህይወትና ንብረት የመታደግ ተግባር ግብራቸው እንዲያደርጉም መልክት አስተላልፈዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አህመድ መሀመድ በበኩላቸው፣ ሰልጣኞቹ በእሳት አደጋ መከላከል፣ በፍለጋና ማዳን እንዲሁም በሌሎች በድንገተኛ አደጋ ምላሽ አሰጣጥ ዙሪያ ስልጠና ያጠናቀቁ ናቸው ብለዋል።
ይህ ስልጠናም የሰራተኞችን አቅም በመገንባት ብቁና ንቁ ሆነው አደጋዎች ሲከሰቱ የሰው ህይወትን እና ንብረትን መታደግ ላይ ብቻ ሳይሆን የአደጋ ተጋላጭ ስፍራዎችን በጥናት በመለየት ፈጣን ምላሽን የሚሰጡ ባለሙያዎችን ለማፈራት ያለመ መሆኑንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
በራሄል አበበ