የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የዓድዋን ታላቅ አደራ በደሙና በአጥንቱ ተሸክሞ የሚገኝ የታሪክና የጀግንነት ውጤት ነው – ኢንጂነር አይሻ መሀመድ

You are currently viewing የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የዓድዋን ታላቅ አደራ በደሙና በአጥንቱ ተሸክሞ የሚገኝ የታሪክና የጀግንነት ውጤት ነው – ኢንጂነር አይሻ መሀመድ

AMN – የካቲት 23/2018 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የዓድዋን ታላቅ አደራ በደሙና በአጥንቱ ተሸክሞ የሚገኝ የታሪክና የጀግንነት ውጤት መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ተናገሩ፡፡

130ኛው የዓድዋ ድል በዓል የምናከብረው “ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩሕ አድማስ” በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ነው፡፡

ሚኒስትሯ ባደረጉት ንግግር፣ መከላከያ ሠራዊት የሀገር ሉዓላዊነትና የሕዝብን ሰላም በጽኑ መሠረት ላይ ከማቆም ባለፈ በአፍሪካ አሕጉር ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የነጻነት ዘብ በመሆን የማይተካ መስዋዕትነት እየከፈለ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ዓድዋ ለሠራዊታችን የታሪክ ማስታወሻ ሳይሆን ዛሬም በመላው አባላቱ የጀግንነት ወኔ፣ በዲስፕሊኑና በአይበገሬነቱ ውስጥ ሕያው ሆኖ የሚኖር የሁልጊዜም ድንቅ የድል ስንቅ ነው ብለዋል።

በዓሉን ስናከብር በአባቶቻችን የነጻነት ገድል ላይ በጽኑ ቆመን የአሁኑን ትውልድ ወደ ላቀ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትና ወደ ብሩሕ አገራዊ ከፍታ የምናሸጋግርበት፣ የታሪክ አደራችንን በስራና በትጋት የምንወጣበት አዲስ የድል ምዕራፍ መሆኑን ልናረጋግጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ትላንት በዓድዋ ተራሮች ላይ የተገኘው ድል ዛሬ በልማትና በብልጽግና ለምናስመዘግበው ድል ዋነኛ የሥነ-ልቦና ስንቃችን ነው ብለዋል፡፡

የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፣ ይህን አኩሪ ታሪክ ለመጪው ትውልድ በሥራና በውጤት የታጀበ ኩራትን በማውረስ ዳግም ልናድሰው ቃል እንገባለን ነው ያሉት።

በታደሠ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review