የዓድዋ ድል ያስተማረን ትልቁ ቁምነገር በሀገር ሉዓላዊነትና በብሔራዊ ክብር ሳንለያይ በጋራ ልንቆም እንደሚገባን ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing የዓድዋ ድል ያስተማረን ትልቁ ቁምነገር በሀገር ሉዓላዊነትና በብሔራዊ ክብር ሳንለያይ በጋራ ልንቆም እንደሚገባን ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – የካቲት 23/2018

የዓድዋ ድል ያስተማረን ትልቁ ቁምነገር ኢትዮጵያውያን በውስጣዊ ጉዳዮቻችን ምንም እንኳን ልዩነቶች ቢኖሩንም፣ በሀገር ሉዓላዊነትና በብሔራዊ ክብር ሳንለያይ በጋራ ልንቆም ይገባናል ብለዋል የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡

130ኛው የዓድዋ ድል በዓል “ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ” በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ይገኛል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበዓሉ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የዓድዋ ጀግኖች ልዩነቶቻቸውን እንዲሁም ቅሬታዎቻቸውን ወደ ጎን ትተው በአንድነት ሆነው በደምና በአጥንታቸው ኢትዮጵያን የማትደፈር ሀገር አድርገው አጽንተው አቁመዋታል፤ በዚህም ክብር አስረክበውናል ብለዋል።

የዚህ ዘመን ትውልድ፣ በተለይም ወጣቱ ይህን የጀግንነት መንፈስ ተላብሶ ልዩነቱን በሰለጠነ መንገድ በውይይት እየፈታ፣ ለብሔራዊ ጥቅም እና ለሀገር ክብር በጋራ ዘብ የመቆም ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለበት ማስተዋል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ከእኛ የሚጠበቀው ከጦር ጀግንነት ባሻገር ወደ ልማት አርበኝነት እየተደረገ ባለው ጉዞ የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ጀግንነት በጦር ሜዳ ወራሪን ማሸነፍ ብቻ አይደለም ያሉት ከንቲባዋ፣ ዛሬም ጀግንነት ማለት ድህነትን፣ ኋላቀርነትን እና መከፋፈልን በጀግንነት ማሸነፍን እንደሚያካትት ጠቅሰዋል፡፡

የዓድዋ ጀግኖች በክቡር መስዋዕትነት ሀገር እንዳስከበሩ ሁሉ፣ እኛም የሀገራችንን ሉዓላዊነት ከየትኛውም ትንኮሳ ተከላክለን በጽናት፣ በላባችን፣ በዕውቀታችን የሀገራችንን ብልጽግና ማረጋገጥ እንደሚጠበቅብን አስረድተዋል፡፡

እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች፣ የስንዴ አብዮት፣ ከልመናና ከተረጂነት ራሳችንን ወደ መቻል እስከመላክ፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ ከተማችን አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ አበባ የማድረግ የትራንስፎርሜሽን ሥራዎች እና የተጀመሩ ሌሎች የልማት ሥራዎች ጉዞ ሁሉ የአዲሱ ዘመን የዓድዋ ድሎቻችን ናቸው ብለዋል፡፡

እነዚህ የልማት ድሎች ለቀጣዩ ትውልድም ውርስ መሆናቸውንም የገለጹት ከንቲባዋ የተዘጋብንን የባሕር በራችንን በፍትሐዊነት በማስከፈት የቀድሞ አርበኞቻችንን ታሪክ ከመዘከር ባለፈ፣ እኛም በዘመናችን ታላቅ ድርብ ድርብርብ ታሪኮችን ሰርተን ለማለፍ በቁጭት እንነሳ በማለት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በታደሠ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review