AMN- የካቲት 23/2018 ዓ.ም
130ኛው የዓደዋ ድል በዓል በአድዋ ድል መታሰቢያ እየተከበረ ይገኛል፡፡
የበዓሉ የክብር እንግዳ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የአድዋ ድል ለሀገር ፍቅር የሚከፈልን መስዋዕትነት ለዓለም የገለጠ ልዩ የታሪክ ምዕራፍ ነው ብለዋል ።
አድዋ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታም የሚውል መሆኑን አብራርተዋል።
አድዋ ግጭትን ለሚፈልጉና የሰላምን መንገድ ለሚሸሹ አካላት ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ፕሬዝዳንት ታዬ ገልጸዋል።
አድዋን ስናስብ የምናስበው ስለ ጀግንነት ነው፤ ጀግንነት ደግሞ ሰላምን ማረጋገጥ፣ ሕዝብን መጥቀምና ሀገር እንዲበለጽግ ማድረግ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ ድሉ የመቻቻል፣ የሀገር ፍቅር፣ የጥበብና የእውቀት መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ የአድዋ ድል ትርጉም ነፃነትን በብልጽግናን ለትውልድ ማስተላለፍና ኩራት የሚሰጡ ሥራዎችን መሥራት መሆኑን አስገንዝበዋል።
አድዋን ስናስብ የአባቶቻችንን እና የእናቶቻችንን መስዋዕትነት ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ የነበራቸውን ራዕይ ጭምር መሆኑን በመጥቀስ፤ የአሁኑ ትውልድ በታሪክ የተሰጠንን አስተማማኝ የባህር በር የማግኘት መብት ለማረጋገጥ ትግሉን መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
አስተማማኝ እና ዘላቂ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ የአድዋ ጀግኖች ያወረሱን አደራና ከሀገር ሉዓላዊነት የማይለይ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ እጣ ፈንታ የሚረጋገጠውና የአድዋ ድል ግብ የሚሳካው፣ የትውልዱ የህልውና ጥያቄ የሆነው የባህር በር ጉዳይ ምላሽ ሲያገኝ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ ይህንንም እውን ለማድረግ መተባበር አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በቶለሳ መብራቴ