የዓድዋ ድል የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ፋና ወጊና የኢትዮጵያውያን የአልበገር ባይነት ማሳያ ነው- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

You are currently viewing የዓድዋ ድል የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ፋና ወጊና የኢትዮጵያውያን የአልበገር ባይነት ማሳያ ነው- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

AMN- የካቲት 23/2018 ዓ.ም

130ኛው የዓድዋ የድል በዓል “ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ” በሚል መሪ ቃል በዓድዋ ድል መታሰቢያ በተለያዩ ደማቅ መርሐ ግብሮች ተከብሯል።

በበዓሉ አከባበር ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ የዓድዋ ድል የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ፋና ወጊ ከመሆኑም ባለፈ፣ የኢትዮጵያውያን የጸና የአልበገር ባይነት ስሜት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢታማዦር ሹሙ አክለውም፣ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ለባዕድ ቀንበር ላለመገዛት፣ ሉዓላዊነታቸውንና ነፃነታቸውን ላለማስደፈር በጀግንነትና በአንድነት የቆሙበት የታሪክ ምዕራፍ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ድሉ ጥቁር ህዝቦች ታሪክ መስራት አይችሉም የሚለውን የፋሽስቶች የተሳሳተ ትርክት የሰበረና ለመላው የዓለም ጥቁር ህዝቦች ኩራት የሆነ አኩሪ ድል መሆኑንም አብራርተዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ባስተላለፉት መልዕክት በህዝብና በፋሽስት ስርዓት መካከል ያለውን ልዩነት አጉልቶ መመልከት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የጣሊያን ህዝብ የሮም ስልጣኔ ታሪክ ባለቤትና የኢትዮጵያ ወዳጅ መሆኑን የጠቀሱት ኢታማዦር ሹሙ፤ በዓድዋ ጦር ግንባር የተሸነፈው የፋሽስት ገዢ መደብ እንጂ የጣሊያን ህዝብ አለመሆኑን በመጠቆም፣ የታሪክ ተንታኞዎች ይህንን ሀቅ ለይተው ሊረዱ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በሌላ በኩል፣ ፋሽስት ጣሊያን የዓድዋ ሽንፈት ሳይዋጥለት በ1928 ዓ.ም በዘመናዊ የጦር መሳሪያና በመርዝ ጭስ የታገዘ ወረራ ቢፈጽምም፤ ጀግኖች አርበኞች ለአምስት ዓመታት በዱር በገደል ባደረጉት ተከታታይ ውጊያ ጠላትን በማዳከም አገራቸውን ለሁለተኛ ጊዜ ነፃ ማውጣታቸውን አስታውሰዋል።

የወቅቱ የመከላከያ ሰራዊት አመራሮችና አባላትም የነዚህን ታላላቅ አርበኞች የአገር ፍቅር ስሜትና ወኔ በመውረስ፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በጽናት ለማስቀጠል በቁርጠኝነት እየታገሉ እንደሚገኙ አረጋግጠዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review