AMN- የካቲት 23/2018 ዓ.ም.
የተለያዩ የአለም ሃገራት ኤምባሲዎች እና አምባሳደሮች ለመላው የጥቁር ህዝብ የነጻነት ተምሳሌት ለሆነው 130ኛው የዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ለ130ኛው የዓድዋ ድል በዓል በሰላም አደረሳችሁ ሲል መልዕክት አስተላልፏል፡፡
ኤምባሲው በመልዕክቱ በኢትዮጵያ የጀርመን አምበሳደር ቢርጊት ኦሪ የኢትዮጵያን ልዩ ታሪክ፣ ነፃነት የሚዘክረውን እና አስደናቂ የሆነውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ መጎብኘታቸው አስታውቋል።
በኢትዮጵያ የካናዳ ኤምባሲ ባስተላለፈው መልዕክት ለታሪካዊዉ የዓድዋ ድል መሠረት የሆነውን የኢትዮጵያውያን ጀግንነት፣ አንድነት እና ጽናት በአክብሮት እንዘክራለን ብሏል፡፡
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የዓድዋ ድል ታሪካዊ ክስተት የኢትዮጵያውያንን የጽናት መንፈስ ያረጋገጠ፤ ለመላው አፍሪካ የነፃነት ትግል መነሻ ሆኗል ነው ያሉት፡፡
በኢትዮጵያ የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ ፣ የሲውድን ፣ የህንድ እና ሌሎች ኤምባሲዎች ለ130ኛው የዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የዲፕሎማሲ ማዕከል በሆነችው አዲስ አበባ በቅርቡ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደረጉት የቱርክዬና የእስራኤል ፕሬዝዳንት እንዲሁም የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በዓድዋ ድል መታሰቢያ የአበባ ጉንጉን ማኖራቸው ይታወሳል ፡፡
በትዝታ መንግስቱ