AMN- የካቲት 24/2018 ዓ.ም
ብዙዎቻችን ኮምፒውተር ወይም ስልክ ላይ ለረጅም ሰዓታት ስናተኩር የዓይን መቆርቆር ወይም መቅላት ያጋጥመናል።
ይህ ሁኔታ የዓይን መድረቅ ሊሆን ይችላል በማለት የዓይን ስፔሻሊስት ዶክተር ልዩ ግርማ ስለ ሕመሙ መንስኤዎች እና በቀላሉ ስለምንከላከልባቸው መንገዶች በዝርዝር ያብራራሉ።
የዓይን መድረቅ የሚከሰተው የሚመረተው እንባ ሲያንስ ወይም ከሚፈለገው በታች ሲመረት ነው የሚሉት ባለሙያዋ፣ ዓይናችን ማግኘት ከሚገባው መጠን በታች የእንባ ፈሳሽ ሲያገኝ ወይም ደግሞ የሚመረተው እንባ በፍጥነት በሚተንበት ጊዜ መሆኑን ያነሳሉ።
የዓይን እንባ ዝም ብሎ ፈሳሽ ብቻ ሳይሆን በሶስት ንብርብሮች የሚመረት መሆኑን በመጥቀስም፣ እነዚህ ንብርብሮች በተለያዩ ምክንያቶች ሚዛናቸውን ካጡ ዓይናችን ለድርቀት ይጋለጣል ይላሉ።

የዓይን መድረቅ መንስኤዎች
የዓይን መድረቅ በተፈጥሮ ወይም በአኗኗር ዘይቤያችን ምክንያት ሊከሰት እንደሚችል የሚናገሩት ዶ/ር ልዩ፣ በአካባቢ ሁኔታ፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በመድኃኒቶች እና በጤና ችግሮች ሊከሰት እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡
ይህም ከፍተኛ ንፋስ፣ ወበቅ ወይም ደረቅ አየር ባለበት ቦታ መኖር፣ በምናውቀውም ሆነ በማናውቀው ሁኔታ ስልክ ወይም ኮምፒውተር ላይ አተኩረን ስናይ ዓይናችንን የመጨፈንና የመግለጥ መጠናችን ስለሚቀንስ እንባ የመትነን አጋጣሚ ይፈጠራል ይላሉ።
ሌላው ለሌሎች ሕመሞች የሚወሰዱ አንዳንድ መድኃኒቶች እና የቤተሰብ የጤና ታሪክ እና የእንባ አመንጪ እጢዎች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ለዓይን መድረቅ መንስኤዎች እንደሆኑ ይናገራሉ።
ምልክቶች

የዓይን መድረቅ ያለበት ሰው ከሚያሳያቸው ምልክቶች መካከል፤ የዓይን መቆርቆር (እንደ አሸዋ ያለ ነገር ውስጥ እንዳለ ሆኖ መሰማት)፣ የዓይን መቅላት፣ ከፍተኛ የሆነ ምቾት ማጣት፣ የዓይን ቀሻሻ መሰል ስሜቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
መከላከያ እና ሕክምናው
ዶክተር ልዩ ግርማ ሕመሙን ለመከላከልና ለማከም፣ ኮምፒውተር ላይ ለሚሰሩ ሰዎች በየመሃሉ (ለምሳሌ በየ 20 ደቂቃው) አይንን ደጋግሞ በመጨፈንና በመግለጥ ራቅ ወዳለ ቦታ በማየት ዓይንን ማራስ ይቻላል ይላሉ።
ከፍተኛ ንፋስ ወይም ፋን ባለበት ቦታ አለመቀመጥ፤ በባለሙያ በሚታዘዝ መተኪያ የእንባ ጠብታ ዓይንን ማለስለስም ሌላው መከላከያ መንገድ እንደሆነም ያብራራሉ።
ችግሩ ከቀጠለ ምርመራ በማድረግ የእንባውን መጠን ማረጋገጥ ይገባል የሚሉት ዶክተር ልዩ፣ እንደ አስፈላጊነቱ እስከ ቀዶ ጥገና የሚደርሱ የሕክምና አማራጮችም አሉ ብለዋል።
ማንኛውም ዓይነት የዓይን ምቾት ማጣት ሲሰማዎት በራስዎ መድኃኒት ከመግዛት ይልቅ፣ ወደ ዓይን ሕክምና ባለሙያ በመሄድ ትክክለኛውን መንስኤ ማወቅ ለዓይንዎ ጤና ወሳኝ ነው ሲሉም ይመክራሉ።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ