AMN – የካቲት 23/2018 ዓ.ም.
በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወረ ቢሮዎች ውስጥ በመግባት ላፕቶፖችን፣ ታፕሌቶችንና የሞባይል ስልኮችን ሲሰርቅ የነበረን ግለሠብ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር ከተደበቀበት ቦታ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።
ቢኒያም ሱራፌል የተባለው ግለሰብ በተለያየ ቢሮዎች ውስጥ በመግባት ላፕቶፖችን፣ ታፕሌቶችንና የሞባይል ስልኮችን ሲሰርቅ የነበረ ሲሆን በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 4 ልዩ ቦታው አርሴማ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ተከራይቶ ከተደበቀበት መኖሪያ ቤት በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል።
ተጠርጣሪው ከዚህ ቀደም በከተማዋ ባሉ የተለያዩ ቢሮዎች በመግባት የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን ሲሰርቅ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያና (Citizen engagement Application) EFPApp እንዲሁም በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ጥቆማዎች መቅረባቸውን ፖሊስ አስታውሷል።
ከዚህ ቀደም ተጠርጣሪው ሳይያዝ እንደተያዘ ተደርጎ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲገለጽ የነበረው ሀሰተኛ መረጃ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር ለማዋል አስቸጋሪ ቢያደርገውም ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ጭምር ክትትል ሲደረግ ቆይቶ በዛሬው ዕለት በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል።
ግለሠቡ ከዚህ ቀደም ወንጀል ፈጽሞ የተሠወረባችሁ አመልካቾችም አዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ በአካል በመምጣት መረጃ መስጠት እንደምትችሉ ጥሪ ያቀረበው ፖሊስ አንዳንድ ግለሰቦች የሚለቁትን የሀሠት መረጃ ከማጋራት ይልቅ ኅብረተሰቡ ከፖሊስ የሚወጡ መረጃዎችን እንዲከታተል መምሪያው ለአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በላከው መረጃ ገልጿል።