የአድዋ ድል መታሰቢያ ትውልድን ያስታረቀ ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing የአድዋ ድል መታሰቢያ ትውልድን ያስታረቀ ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ
  • Post category:ታሪክ

AMN – የካቲት 24/2018 ዓ.ም

የአድዋ ድል መታሰቢያ የኢትዮጵያውያንን አንድነትና እርቅ የሚያጠናክር ታላቅ የታሪክ ማዕከል መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከንቲባዋ ይህን ያሉት 130ኛውን የአድዋ ድል በዓል፣ የአድዋ ዘማቾች መነሻ በሆነውና የጀግኖችን የተጋድሎ ታሪክ በሚመጥን መልኩ እዲዘከር በተገነባው የአድዋ ድል መታሰቢያ ከከተማዋ ወጣቶች ጋር በፓናል ውይይት ባከበሩበት ወቅት ነው።

የአድዋ ድል መታሰቢያ የኢትዮጵያን እውነተኛ ታሪክ ለትውልድ በማስተላለፍ ረገድ ካለው ፋይዳ ባሻገር፣ በተለያዩ የታሪክ እሳቤዎች ዙሪያ ይነሱ የነበሩ ልዩነቶችን በማክሰም የሕዝቦችን አንድነትና እርቅ እያጠናከረ መሆኑን ከንቲባዋ ተናግረዋል።

መታሰቢያው ምንም ዓይነት አዲስ ትርክት ሳይጨመርበት፣ እውነተኛው ታሪክ ተሰባስቦ የተሰነደበት በመሆኑ በትውልዱ መካከል የነበሩ የሃሳብ ግጭቶችን በማስቀረት የታሪክ እርቅ እንዲፈጠር እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

ከንቲባ አዳነች አክለውም፤ የአድዋ ድል የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ የያዘ በመሆኑ፣ መታሰቢያው የሚያጣላ ሳይሆን ሕዝቦችን የሚያሰባስብና የሚያቀራርብ ታላቅ የታሪክ አሻራ ሆኖ ያገለግላል ሲሉ ገልጸዋል።

ከተለያየ ዓለም ክፍል የሀገር መሪዎች ወደ ኢትዮጵያ በሚመጡበት ወቅት በመታሰቢያው በመገኘት ለሰማዕታት አበባ በማስቀመጥና ታሪኩን በመማር ለሀገሪቱ ያላቸውን ክብር እንዲገልጹ ዕድል መፍጠሩንም አብራርተዋል።

ይህ የታሪክ ማዕከል “ከሁሉም፣ በሁሉም፣ ለሁሉም” የምትሆን ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ፣ የመደመር እሳቤን በተግባር በማሳየት ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review