AMN – የካቲት 24/2018 ዓ.ም
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ፍትሓዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲካሄድ የሴቶች ድርሻ የጎላ መሆኑን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የፓርቲው ዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
አቶ አደም ፋራህ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ዛሬ በሰላም ሚኒስቴር እና በሴቶች አደረጃጀቶች አስተባባሪነት “በሴቶች ተሳትፎ የጸናችና የበለፀገች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀ ሀገራዊ የንቅናቄ ማጠቃለያ መድረክ ላይ መገኘታቸውን ገልጸዋል።
ይህ መድረክ በመጪው ጠቅላላ ምርጫ የሴቶችን ሚና ለማጎልበት እና ተሳትፏቸውን ለማሳደግ ያለንን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየንበት ታላቅ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል ብለዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት መረጋገጥ የሰጠነው ልዩ ትኩረት በሴቶች የፖለቲካ ውሳኔ ሰጪነት፣ በኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ በትምህርት፣ በጤና እና በማኅበራዊ ጥበቃ ዘርፎች ተጨባጭ ፍሬዎችን እያፈራ ይገኛል ሲሉም አክለዋል።
ይህ ስኬት ጅምር እንጂ ፍጻሜ ባለመሆኑ፣ ሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚ የሚገቱ ስብራቶችን የመጠገንና እድሎችን የማስፋት ሥራችን በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
በተለይም ሴቶችን የዴሞክራሲያችን ጽኑ ምሰሶ ለማድረግ የጀመርናቸውን ጥረቶች ለማጠናከር በቁርጠኝነት የምንንቀሳቀስ ይሆናል።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ፍትሓዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲካሄድ በየደረጃው የምትገኙ የሀገራችን ሴቶች የበኩላችሁን የዜግነት ድርሻ እንድትወጡ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል።