ከዓድዋ እስከ ህዳሴ – የኢትዮጵያውያን የአሸናፊነት እና የአንድነት ጉዞ

You are currently viewing ከዓድዋ እስከ ህዳሴ – የኢትዮጵያውያን የአሸናፊነት እና የአንድነት ጉዞ

AMN – የካቲት 24/2018 ዓ.ም

የዓድዋ ድል የኢትዮጵያዊያን የጽናት፣ የጋራ መቆምና የአንድነት ህያው ማሳያ ነው። ይህ ድል አድራጊ መንፈስ ዘመናትን ተሻግሮ፣ በዛሬው ትውልድ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በድምቀት ተደግሟል።

የታሪክ መምህሩ አቶ በላይ ስጦታው ለኤ ኤም ኤን እንደገለጹት፣ የዓድዋ ድል የተገኘው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለምንም ልዩነት በአንድነት በመቆሙ ነው።

የንጉሠ ነገሥቱን የክተት አዋጅ ተከትሎ፣ ኢትዮጵያዊያን ከያሉበት የሀገሪቱ ጥግ ሁሉ በወኔ በመተመም ያኔ ኃያል የነበረውን የጣልያን ወራሪን ጦር ድል ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

ይህ ስኬት በመሣሪያ ብልጫ ሳይሆን፣ በሕዝብ የማይበገር አንድነትና ተጋድሎ የተገኘ መሆኑን መምህሩ አስረድተዋል። በአሁኑ ትውልድም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የዘመናችን “የዓድዋ ድል” ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል ብለዋል።

በግድቡ ግንባታ ሂደትም መላው ኢትዮጵያዊያን የዘር፣ የሃይማኖት ወይም የኢኮኖሚ ልዩነት ሳይበግራቸው አቅማቸውን በማስተባበራቸው ግድቡ ለዚህ ስኬት መብቃቱንም መምህሩ አውስተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የመንግሥት አካላት በዓለም አቀፍ መድረክ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ትግል በማድረግ፣ ተጽዕኖዎችን በመቋቋም እና ያለምንም የውጭ ብድር በራስ አቅም ፕሮጀክቱን ማሳካት መቻሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ አድናቆትን ያተረፈ ተግባር ነው ብለዋል።

አቶ በላይ አክለውም፣ የዓድዋ ድልና የሕዳሴው ግድብ ስኬት የአሁኑን ትውልድ የሚያኮሩ ብቻ ሳይሆኑ፣ በአባቶቻቸው የታሪክ ቅብብሎሽ ላይ በመመሥረት ለወደፊት የላቀ ሥራ እንዲሠሩ የሚያነሳሱ የኃይል ምንጮች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ፣ ኢትዮጵያዊያን የዓድዋን መንፈስ በመድገም ማንኛውንም ግዙፍ አገራዊ ፕሮጀክት በራሳቸው አቅም ማሳካት እንደሚችሉ ለዓለም ያሳዩበት ታሪካዊ ክስተት መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ስኬት ለቀጣዩ ትውልድ መነሳሳትን ከመፍጠሩም በላይ፣ አፍሪካውያን ያለ ውጭ እርዳታ በራሳቸው ጥረት እና አቅም ተአምር መሥራት እንደሚችሉ ትልቅ ትምህርት የሰጠ መሆኑን አቶ በላይ አስገንዝበዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review