ኒውካስትል ከ ማንችስተር ዩናይትድ ፣ አስቶንቪላ ከ ቼልሲ ፦ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎ ለማግኘት የሚደረጉ ፍልሚያዎች

You are currently viewing ኒውካስትል ከ ማንችስተር ዩናይትድ ፣ አስቶንቪላ ከ ቼልሲ ፦ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎ ለማግኘት የሚደረጉ ፍልሚያዎች

AMN- የካቲት 25/2018 ዓ.ም

በ29ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ከሚከናወኑ ጨዋታዎች መካከል በቀጣይ የውድድር ዓመት የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎ ለማግኘት እየተጉ የሚገኙት ቡድኖች የሚያደርጓቸው ግጥሚያዎች ይጠበቃሉ።

ውጤታማ ጉዞ ላይ የሚገኘው ማንችስተር ዩናይትድ ወደ ሴንት ጀምስ ፓርክ አቅንቶ ከኒውካስትል ዩናይትድ ጋር ይጫወታል።

ማይክል ካሪክን የክለቡ አሰልጣኝ አድርጎ ከሾመ በኋላ ተከታታይ ድል እያስመዘገበ የሚገኘው ዩናይትድ በሳምንቱ መጨረሻ ክርስታል ፓላስን ማሸነፉ በግብ ክፍያ በልጦ 3ኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አስችሎታል።

ኒውካስትል ዩናይትድ የባለፉት ጥቂት ዓመታት ጥንካሬው አብሮት አይገኝም። በተለይ በፕሪምየር ሊጉ እያስመዘገበው ያለው ውጤት የተጠበቀውን ያህል አይደለም። የኤዲ ሀው ቡድን በ36 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ማንችስተር ዩናይትድ በሴንት ጀምስ ፓርክ በቅርብ ዓመታት ጥሩ ውጤት አላስመዘገበም። ባለፈው ዓመት 4ለ1 የተረታበትን ጨምሮ በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ተሸንፏል።

በአጠቃላይ ከሰባት የመጨረሻ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ኒውካስትል አራቱን አሸንፏል። ማንችስተር ዩናይትድ ሁለቱን ብቻ በድል ተወጥቷል።

የዛሬ ፍልሚያቸው ምሽት 5:15 ሲል ይጀምራል።

በጨዋታው በማንችስተር ዩናይት በኩል ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ አይመለስም። ሉክ ሾው እና ሃሪ ማጓየር መግባታቸው ገና አልተረጋገጠም።

ኒውካስትል ዩናይትድ ያለ አምበሉ ቡርኖ ጉማይሬሽ ለመጫወት ይገደዳል።

ሌላው የምሽቱ ተጠባቂ ጨዋታ በቪላ ፓርክ አስቶንቪላ ቼልሲን የሚያስተናግድበት ነው።

ለወራት የዋንጫ ተፎካካሪ መስሎ የነበረው አስቶንቪላ አሁን ላይ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎ ለማግኘት የበለጠ መትጋት አለበት። ለቪላ ተስፋ የሚሰጠው ትናንት ምሽት ሊቨርፑል በዎልቭስ መሸነፉ ነው።

ቼልሲም እንደቪላ ሁሉ ወጥነት የጎደለው ቡድን ሆኗል። በሊያም ሮሲኒዮር እየተመራ የመጀመሪያ የፕሪሚየር ሽንፈቱን በአርሰናል የቀመሰው ቼልሲ የቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎውን ላለማጣት የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ግዴታው ነው።

ቪላ 51 ነጥብ ሲሰበስብ ፣ ቼልሲ ደግሞ 45 ነጥብ አለው።

ለሁለቱም ቡድኖች ወሳኝ የሆነው ጨዋታ ምሽት 4:30 የሚጀምር ይሆናል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review