የጥርስ ህመምን ችላ ማለት የሚያስከትለው አደጋና መፍትሄዎቹ

You are currently viewing የጥርስ ህመምን ችላ ማለት የሚያስከትለው አደጋና መፍትሄዎቹ
  • Post category:ጤና

AMN- የካቲት 25/2018 ዓ.ም

የጥርስ ህመም በድንገት ተከስቶ የሰውን ልጅ የዕለት ተዕለት የሥራና የኑሮ እንቅስቃሴ ከሚያስተጓጉሉ የጤና እክሎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳል።

ብዙዎች ህመሙ ጸንቶ እንቅልፍ እስከሚነሳቸው ድረስ ወደ ህክምና ተቋም የመሄድ ልምድ ባይኖራቸውም፣ የጥርስ ህመምን ችላ ማለት ግን ከጥርስ ጉዳት ባለፈ ለከፋ የጤና ችግር ሊዳርግ ይችላል።

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የጥርስ ሀኪም የሆኑት ዶ/ር ሰውዳ ሲራጅ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ የጥርስ ህመም በብዙ ምክንያቶች ሊከሰት የሚችል ሲሆን፤ በተለይም የጥርስ መቦርቦር፣ የድድ በሽታ እና የጥርስ አበቃቀል መዛባት ዋነኞቹ መንስኤዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።

በአፍ ውስጥ የሚገኙ ባክቴሪያዎች የምንመገበው ምግብ ከስኳርና ከካርቦሃይድሬት ጋር በመቀላቀል ጥርስን የሚበላ አሲድ እንደሚያመነጩ የገለጹት ባለሙያዋ፣ ይህም ቀስ በቀስ ጥርስ እንዲበሰብስ በማድረግ ለከፍተኛ ህመም እንደሚዳርግ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የድድ ማበጥና መድማት ችላ ከተባለ ኢንፌክሽኑ ወደ ጥርስ ስር በመዝለቅ መንጋጋንና አጥንትን እስከማዳከም ሊደርስ እንደሚችል ዶ/ር ሰውዳ ያስገነዝባሉ።

የጥርስ ኢንፌክሽን በደም ውስጥ በመዘዋወር ለልብና ለሌሎች የውስጥ አካላት ህመም ምክንያት ሊሆን ስለሚችል፣ ማንኛውም የህመም ስሜት ሲሰማ በአፋጣኝ ወደ ህክምና ተቋም መሄድ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በአሁኑ ወቅት የጥርስ ህክምና ቴክኖሎጂ በመዘመኑ የተጎዳን ጥርስ ሳይነቅሉ የማዳን እድሉ ሰፊ መሆኑን ባለሙያዋ ጠቁመዋል።

እንደ ህመሙ ደረጃና አይነት የሚሰጡ የህክምና አማራጮችም የተለያዩ ሲሆኑ፣ ጥርሱ በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድቶ ነርቭ ላይ በደረሰ ጊዜ የነርቭ ህክምና በማድረግ ጥርሱ ሳይነቀል እንዲድን ይደረጋል።

በሌላ በኩል በትንሹ የተቦረቦሩ ጥርሶችን በማጽዳትና በሜርኩሪ አልባ የጥርስ ሙሌቶች በመሙላት ጥርሱ የቀድሞ ጥንካሬውንና ውበቱን እንዲያገኝ ማድረግ ይቻላል።

ለድድ ጤንነት ሲባልም በየስድስት ወሩ በባለሙያ የታገዘ የጥርስ ማጽዳት ስራ ማከናወን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ዶ/ር ሰውዳ ይገልፃሉ።

ዶ/ር ሰውዳ ሲራጅ አክለውም፤ ጥርስን በቀን ሁለት ጊዜ መቦረሽና በየጊዜው ምርመራ ማድረግ የጥርስ ህመምን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ ይመክራሉ።

የሀመሙ ተጠቂዎች ወደ ህክምና ተቋም እስኪሄዱ ድረስ ህመሙን ለማስታገስ በቤት ውስጥ በጨው የፈላ ውሃ መጉመጥመጥ እንዲሁም ተፈጥሯዊ የህመም ማስታገሻ የሆነውን ቅርንፉድ መጠቀም እንደ ጊዜያዊ መፍትሄ ቢጠቀሱም፣ ዘላቂ ፈውስ ለማግኘት ግን የባለሙያ እገዛ የግድ እንደሚል አስረድተዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review