AMN የካቲት 24/2018
ለተሳካ የሀገረ መንግሥት ግንባታ መሠረት የሚጥሉ ጠንካራና ገለልተኛ የዳኝነትና ዴሞክራሲ ተቋማት መገንባት መቻሉን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
ዛሬ “የዳኝነትና ዴሞክራሲ ተቋማት እመርታ፤ ለተሳካ ሀገረ መንግሥት ግንባታ!” በሚል መሪ ሀሳብ በዳኝነትና ዴሞክራሲ ተቋማት ቅንጅት ላይ የሚያተኩር ሀገራዊ መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምሕረት የፍርድ ቤቶች የለውጥ ተግባራትን አስመልክቶ ባቀረቡት የመነሻ ሐሳብ፤ የዳኝነት ነጻነትን ለማጠናከር የሕግ ማሻሻያ መደረጉን ተናግረዋል።
ግልጽነት እና ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ አኳያም ግልጽ ችሎትን የማስፋፋት ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቅሰው፤ ግልጽ ችሎት ከነበረበት 65 በመቶ ወደ 91 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።
የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ባቀረቡት ጽሑፍ፤ ኮሚሽኑ እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እስካሁን ውጤታማ የሚባሉ ሥራዎችን ሰርቷል ብለዋል።
የሀገሪቱን ሁሉንም ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ 93 በመቶ ማካተት መቻሉን ጠቁመው፤ በቀጣይም አጀንዳ መቅረጽና ይፋ ማድረግ እንዲሁም ሀገራዊ ምክክር ማካሄድ ከሚከናወኑ ስራዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስብሳቢ ሜላትወርቅ ሃይሉ የቦርዱን የለውጥ እና ቀጣይ ተግባራት ባቀረቡት ጽሑፍ፤ ቦርዱ ባለፉት ዓመታት ተቋማዊ የሕግ ማሻሻያዎችን በማድረግ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል።
ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የዕጩዎችን ምዝገባ ሙሉ በሙሉ በዲጂታል በማከናወን ማጠናቀቅ መቻሉን ተናግረው፤ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ስልጠና መሰጠት መቻሉንም ገልጸዋል።
ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በስኬታማነት ለማከናወን “ምርጫዬ” የመራጮች መመዝገቢያ የዲጂታል አማራጭ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ ባቀረቡት የመነሻ ጽሑፍ፤ ነጻና ገለልተኛ ተቋም ለመገንባት የአዋጅ ማሻሻያ፣ ደንብና መመሪያዎችን ማሻሻል መቻሉን ገልጸዋል።
ከኦዲት ሽፋን አኳያም የፋይናንሻል ኦዲት መቶ በመቶ ማከናወን መቻሉን በመጥቀስ፤ የክዋኔ ኦዲትንም ከ24 ወደ 41 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።
የኢትየጵያ ሕዝብ ዕምባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕምባ ጠባቂ ስመኝ ውቤ ባቀረቡት ጽሑፍ፤ ከለውጡ ወዲህ በተከናወኑ የለውጥ ስራዎችም ከአሰራርና ከሰው ሃይል አኳያ፣ የሕግ ማሻሻያ ተግባራት፣ ከቴክኖሎጂ አኳያ እንዲሁም ቅንጅታዊ አሰራሮች ተዘርግተው ስኬታማ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
ከቴክኖሎጂ ስራዎች ለግልጸኝነት፣ ለተጠያቂነት፣ ለቅልጥፍና እንዲሁም ለውጤታማነት ምቹ መደላድል መፍጠራቸውን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ባቀረቡት የመነሻ ጽሑፍ፤ ከለውጡ በፊት ኮሚሽኑ ገለልተኛ እና ውጤታማ ያልነበረ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት ምቹ የሕግ ማዕቀፍ፣ አዲስ የሰው ሃብት መዋቅር፣ ብቃትና አቅም ያለው አመራር መፍጠር፣ ሥራን የሚያቀላጥፉ በቴክኖሎጂ የተደገፉ መፍትሔዎች፣ የመረጃ ስርዓት በቴክኖሎጂ የሚመራ መደረጉ እንዲሁም የፋይናንስ ነጻነትን ማረጋገጥ መቻሉን ጠቁመዋል።
የመድረኩ ታሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ተቋማት ነጻና ገለልተኛ ሆነው እንዲደራጁ መደረጉን ማድነቃቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።