AMN የካቲት 25/2018 ዓ.ም
ኤርትራዊያን በሻዕቢያ ምክንያት በሃገራቸዉም ሆነ በተለያዩ ሃገራት በሰላም ሰርተዉ ለመኖር አልቻሉም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በትግርኛ ቋንቋ ከኢዜአ ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ሻዕቢያ በኤርትራም ሆነ ከኤርትራ ዉጪ በዜጎቹ ላይ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን እየፈጸመ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የኤርትራ ህዝብ የስራ ፍቅር ያለዉና ስራ ፈጣሪ ቢሆንም የሚፈልገዉን መንግስት ሊያገኝ አልቻለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሻዕቢያ ልማት እና የስልጣን ሽግግርን ጨምሮ ልጆቹን እና የልጅ ልጆቹን ሳይቀር አያምናቸዉም ብለዋል፡፡
ሻዕቢያ ስልጣን ሲይዝ ከ300 በላይ ፋብሪካዎች ኤርትራ ዉስጥ እንደነበሩ የነበሩ ቢሆንም አሁን ላይ ግን በዚያች ሃገር ሁሉም በሚባል ደረጃ ፋብሪካዎች ወድመዋል፡፡
በወቅቱ ኤርትራ ዉስጥ አስመራ ዩኒቨርስቲ የምትባል አንዲት ዩኒቨርስቲ ነበረች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እሷም ተዘግታለች፤ ኤርትራ እንደ ሀገር አንድም ዩኒቨረስቲ የላትም ብለዋል፡፡
የኤርትራ ህዝብ ሀገሩን ትቶ እየተሰደደ ነዉ፤ ኤርትራም ባዶ እየሆነች ነዉ ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የተሰደዱ ኤርትራዊያን በሄዱበት ሃገር በሰላም ሰርተዉ እንዳይኖሩ ሻዕቢያ ሰላዮችን አብሮ ይልካል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሃገራቸዉም ሆነ በተሰደዱበት ሃገር በሰላም ሰርተዉ ለመኖር መቸገራቸዉንም አንስተዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ