AMN – የካቲት 25/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድርን ለማዘጋጀት ከዓለም አትሌቲክስ ይፋዊ ዕውቅና እና የአዘጋጅነት ዕድል አግኝታለች።
በዚሁ መሠረት ውድድሩን ሚያዝያ 10/2018 ዓ.ም. በአዲስአበባ ለማዘጋጀት በዛሬው ዕለት ዕድል በማግኘት በዓለም አትሌቲክስ ካላንደር ውስጥ መካተት ችላለች።
የዓለም አትሌቲክስ የውድድር ዋና ዳይሬክተር ፒርስ ኦክላጋን በዚህ ወር መጀመሪያ በኢትዮጵያ ይፋዊ የሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ “ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማዘጋጀት በቂ አቅም እንዳላትና የተለያዩ ውድድሮችን ወደ ኢትዮጵያ እናመጣለን ማለታቸው” የሚታወስ ነው።

ውድድሩን የዓለም አትሌቲክስ ከፍተኛ ባለሙያዎች የሚመሩት በመሆኑ ለአገራችን የአትሌቲክስ አሰልጣኞች የልምድ ልውውጥ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።
ውድድሩ ከተለያዩ አገሮች የተወጣጡ አትሌቶች የሚሳተፉበት ከመሆኑ ባሻገር አሸናፊ ለሚሆኑ አትሌቶች ከፍተኛ ሽልማት የሚያገኙበት እንደሚሆን ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ የዚህን ታሪካዊ ዓለም አቀፋዊ ውድድር አዘጋጅነት ዕድል በማግኘቷ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለዓለም አትሌቲክስ የላቀ ምስጋናውን አቅርቧል።
በተጨማሪም ውድድሩ ወደ ሀገራችን እንዲመጣ ከፍተኛ ጥረት ላደረጉት የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከፌዴሬሽኑ ጎን በመቆም አጋርነታቸውን ላሳዩ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ያለውን አክብሮት ፌዴሬሽኑ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ ላይ አስፍሯል።