AMN – የካቲት 25/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በቅርቡ ለምታካሂደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተሳታፊነቱን ያረጋገጠው የህብር ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ምርጫው ሰላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት አስታወቀ።
የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ ስለ ፓርቲያቸው የቅድመ ምርጫ ዝግጅት ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ አድርገዋል። በቆይታቸውም ምርጫው በሰለጠነ መንገድ ተካሂዶ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሁሉ ውጤቱን በፀጋ ሊቀበሉ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሊቀመንበሩ በንግግራቸው ኢትዮጵያ ቀደም ባሉት የምርጫ ታሪኮቿ ካጋጠሟት ግጭቶችና ሁከቶች ያተረፈችው ድህነትን ብቻ መሆኑን አስታውሰዋል።
“አሁን ያለው ትውልድ ካለፉት ስህተቶች ትምህርት መውሰድ አለበት” ያሉት አቶ ግርማ፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የስልጣን ሽግግር መደረግ ያለበት በዲሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ እንደሆነ በአፅንኦት ገልጸዋል።
“የወከልኩት ፓርቲ በምርጫ ቢሸነፍ እንኳ ውጤቱን በፀጋ እቀበላለሁ፤ ምክንያቱም ከብጥበጥና ከሁከት የምናተርፈው ውድመትን እንጂ ዕድገትን አይደለም” ሲሉ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
አሁን ላይ ያለው የመረጃ ተደራሽነት ከቀደሙት ምርጫዎች በተሻለ ሁኔታ ላይ መሆኑን የጠቀሱት ሊቀመንበሩ፣ ይህም ዜጎች በነፃነት መረጃ እንዲያገኙ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
በመሆኑም መራጮች የተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮችን በመጠቀም የፓርቲዎችን ዕቅድና ማኒፌስቶ በሚገባ መርምረው ለሀገር የሚበጀውን እንዲመርጡ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቁመዋል።
ማንኛውም ተፎካካሪ ፓርቲ የሕዝብን ድምፅ የማክበር ግዴታ እንዳለበት የገለጹት አቶ ግርማ፣ ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላም ቢሆን አሸናፊው አካል ካልተመረጡት ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።
“አንድ ሀገር ነው ያለን፣ ለአንድ ሀገር ነው የምንሰራው” ያሉት ሊቀመንበሩ፣ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ለሀገራዊ ዓላማና ለልማት በጋራ መቆም እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በበረከት ጌታቸው