AMN- የካቲት 26/2018 ዓ.ም
የዘመነ የካሜራ ክትትልንና የሰው አልባ ቴክኖሎጂን በመጠቀም፣ የፌደራል ፖሊስ በቦሌ መንገድ የተዘረፈ የውጭ ሀገር ዜጋን ንብረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስመለስ ችሏል።
ድርጊቱን የፈጸሙና ተባባሪ የሆኑ 12 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፣ ተበዳዩም በኢትዮጵያ ፖሊስ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም መደነቃቸውን ገልጸዋል።
ሳቶስ ኩማር የተባሉት ተበዳይ ለኤ ኤም ኤን እንደገለጹት፣ ምሽት ሁለት ሰዓት ተኩል አካባቢ በቦሌ መንገድ ላይ እየተጓዙ ሳለ፣ ሁለት ግለሰቦች ለማኝ መስለው በመቅረብ አዋክበው ስልካቸውን ከኪሳቸው ነጥቀዋቸዋል።
ወዲያውኑ በአቅራቢያው ለነበሩ የፌደራል ፖሊስ አባላት በማመልከታቸው፣ ፖሊሶቹ ወደ ሰው አልባ ፖሊስ ጣቢያ ማዕከል በመውሰድ በካሜራ የታገዘ ክትትል እንዲጀመር አድርገዋል።
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የባምቢስ ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ ኮማንደር ዳንኤል ነሞምሳ፣ የወንጀል ድርጊቱ የተፈጸመው በኮሪደር ልማት አካባቢ በእግር በሚጓዙ ዜጎች ላይ ነው።

ወንጀለኞቹ በቡድን በመሆን አንደኛው ትኩረት በመሳብ ሌሎቹ ደግሞ ስልክ በመንጠቅ እንደሚሰወሩ ገልጸዋል።
ፖሊስ ከቴክኖሎጂ ማዕከሉ የደረሰውን መረጃ ተከትሎ ወዲያውኑ ወንጀሉ ወደ ተፈጸመበት ስፍራ በማቅናት ተጨማሪ የካሜራ ማስረጃዎችን አሰባስቧል።
በዛው ሌሊት 8 ተጠርጣሪዎችን፣ በንጋታው ደግሞ ተጨማሪ 4 ተጠርጣሪዎችን በመያዝ በአጠቃላይ 12 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ከተያዙት ውስጥ ድርጊቱን የፈጸሙትን ሁለት ግለሰቦች በመለየት እና ስልኩን ይዞ የተሰወረውን ሌላ ተጠርጣሪ በክትትል በመያዝ ስልኩ ለባለቤቱ እንዲመለስ ተደርጓል።
ንብረታቸው የተመለሰላቸው ሳቶስ ኩማር፣ ፖሊስ በቴክኖሎጂ ታግዞ የሰጠውን ፈጣን ምላሽ አድንቀዋል።
“በጥቂት ቀናት ውስጥ ስልኬን በማግኘቴ በጣም ተደስቻለሁ፣ አዲስ አበባ በፖሊስ ሰላሟ የተጠበቀ መሆኑን አረጋግጫለሁ” ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ኮማንደር ዳንኤል ነሞምሳ በበኩላቸው፣ ማንኛውም የወንጀል ድርጊት ሲፈጸም ለፌደራል ፖሊስ ማመልከት እንደሚቻል ገልጸው፣ የሀገርን ገጽታ ለመጠበቅ ፖሊስ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ