በአዲስ አበባ 16ኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት የክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ውድድር እየተካሄደ ነው

You are currently viewing በአዲስ አበባ 16ኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት የክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ውድድር እየተካሄደ ነው

AMN- የካቲት 26/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ፤ 16ኛውን የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ምክንያት በማድረግ ያዘጋጀው የከተማ አቀፍ የክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ውድድር በልህቀት ማዕከል እየተካሄደ ይገኛል።

ውድድሩ በዕውቀት እና በክህሎት የታነጸ ብቁ ባለሙያ ለማፍራትና የፈጠራ ሥራዎችን ወደ ገበያ ለማውጣት ያለመ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ የምርታማነት ማሻሻያ የልህቀት ማዕከል ዋና ዲን አቶ አድማሱ በቀለ እንደገለጹት፤ ውድድሩ ከ13 የመንግሥት ኮሌጆች የተውጣጡ 509 ተወዳዳሪዎችን ያሳተፈ ነበር።

በየኮሌጆቹ በተደረገው የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ አሸናፊ የሆኑ 123 ሰልጣኞች ወደ ክላስተር ውድድር ያለፉ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በከተማ ደረጃ ለሚካሄደው የመጨረሻ ውድድር 86 ተወዳዳሪዎች ብቃታቸውን እያሳዩ ይገኛሉ።

እነዚህ ተወዳዳሪዎች በ20 የሙያ አይነቶች የተሰማሩ ሲሆን፣ በተግባር የተደገፈ የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ለባለሙያዎችና ለዳኞች እያቀረቡ ነው።

የዘንድሮውን ውድድር ከወትሮው ለየት የሚያደርገው፣ የሰልጣኞችን ክህሎት ከመመዘን ባለፈ የፈጠራ ውጤቶቻቸውን ለገበያ ለማቅረብ ልዩ ትኩረት መስጠቱ እንደሆነ ተጠቁሟል።

በቀጣይ ቀናትም የቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ በማዘጋጀት የፈጠራ ውጤቶቹ ለሕዝብ እይታ እንዲቀርቡና በቀጥታ ለገበያ እንዲውሉ እንደሚደረግ ዋና ዲኑ አብራርተዋል።

በሥራና ክህሎት ቢሮ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽንና ኢንኩቤሽን አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ በየነ በበኩላቸው፣ እንዲህ ያሉ መድረኮች ሰልጣኞች ከትምህርት ገበታቸው እንደወጡ በቀጥታ ወደ ሥራ ፈጠራና ወደ ገበያው እንዲገቡ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥሩላቸው ገልጸዋል።

በከተማ ደረጃ አሸናፊ ለሚሆኑ ሰልጣኞች በየሁለት ዓመቱ በሚካሄደው ሀገር አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ውድድር ላይ ከተማዋን ወክለው እንዲሳተፉ ይደረጋልም ብለዋል።

በተጨማሪም የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ይበልጥ አሳድገው ወደ ኢንተርፕራይዝ እንዲቀየሩ የድጋፍና የክትትል ሥራዎች እንደሚከናወኑ አቶ ፀጋዬ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ ዘርፉን ሪፎርም በማድረግ፣ ዘርፉ ለከተማዋ ኢኮኖሚና ለኢንዱስትሪው ዕድገት የላቀ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝም ተመላክቷል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review