AMN- የካቲት 26/2018 ዓ.ም
በችግርና በህመም ተስፋ በቆረጠው የአቶ አሸናፊ ቤተሰብ ውስጥ፣ የከንቲባ አዳነች አቤቤ ርህራሄ የታከለበት ድጋፍ አዲስ የብርሃን ጭላንጭል ፈጥሯል። ለ10 ዓመታት አልጋ ላይ የቆየችው ብሌን አሸናፊ፣ አሁን በከንቲባዋ አስተባባሪነት በባለሀብቶች ትብብር የውጭ ሀገር ህክምናዋን ልታገኝ ነው።
ህፃን ብሌን አሸናፊ ለወላጆቿ የመጀመሪያ ልጅ ስትሆን፣ ገና የ40 ቀን ጨቅላ እያለች ባጋጠማት የጭንቅላት ውስጥ ፈሳሽ የጤና እክል ምክንያት፣ እድሜዋ 10 ቢሞላም እንደ እኩዮቿ መቦረቅና መማር አልቻለችም። በዚህ ፈታኝ ጉዞ ውስጥ ግን ብርቱው አባቷ አቶ አሸናፊ አሰፋ፣ የከተማ ፅዳት እየሰራ ልጁንና አረጋዊ እናቱን በመንከባከብ የብዙዎችን ልብ የነካ የፅናት ተምሳሌት ሆኗል። አቶ አሸናፊ ልጁን በቅርበት ለመንከባከብ ሲል ብቻ የነበረውን የሹፌርነትና ሌሎች ስራዎች ትቶ፣ በዝቅተኛ ገቢ የፅዳት ሰራተኛ ሆኖ ለዓመታት ሲታገል ቆይቷል።

የዚህን ቤተሰብ ታሪክ በማህበራዊ ሚዲያ የተከታተሉት የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በጉዳዩ እጅግ በመነካት የችግሩ ተካፋይነታቸውን በተግባር አሳይተዋል። ከንቲባዋ የመንግስትን በጀት ብቻ ከመጠበቅ ይልቅ፣ ባለሀብቶችን በማስተባበር ለህፃኗ ህክምና የሚሆን ቋሚ መፍትሄ አምጥተዋል።
በዚህም መሰረት ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እና ከባለቤቱ ሼክ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ ጋር በመነጋገር፣ ለህፃን ብሌን የውጭ ሀገር ህክምና የሚውል 4 ሚሊየን ብር ድጋፍ እንዲገኝ አድርገዋል። ከንቲባዋ በአቶ አሸናፊ ጠባብ የኪራይ ቤት ድረስ በአካል በመገኘት ድጋፉን አስረክበዋል።
“ህክምናውን ለማገዝ ሁልጊዜ ከመንግስት በጀት ብቻ መጠበቅ የለብንም ብለን ነው የምናስበው፤ ስለዚህ ባለሀብቶችን ጠየቅን፤ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጥሪያችንን ተቀብሎ ይህንን ድጋፍ አድርጓልም ብለዋል። አሁን የጤና ቢሯችን አስፈላጊውን ሰነድ እያዘጋጀ ሲሆን፣ አባቷ በአስቸኳይ ይዟት ሄዶ እንዲያሳክማት እናደርጋለን” ነው ያሉት።

የህፃኗን ህክምና ብቻ ሳይሆን፣ ቤተሰቡ የሚኖርበትን አስቸጋሪ ሁኔታም የተመለከቱት ከንቲባዋ፣ ስድስት ቤተሰብ በአንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ እንደሚኖርም ተረድተዋል። ይህንንም ተከትሎ ህፃኗ ወደ ውጭ እስክትሄድና ስትመለስም የተሻለ እንክብካቤ እንድታገኝ፣ ለፊዚዮቴራፒ አመቺ የሆነና ቤተሰቡን የሚመጥን አዲስ የመኖሪያ ቤት ቁልፍ ለባለቤቱ አስረክበዋል።
ይህ ድጋፍ ያልጠበቁት መሆኑን የገለጹት አቶ አሸናፊ፣ በደስታ በእንባ ታጅበው ለከንቲባዋ እና ለባለሀብቱ ያላቸውን ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሚኒሊክ ሆስፒታል ለሚሰጠው የነጻ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት ሚድሮክ እያደረገ ያለውን ድጋፍ በማስታወስ፣ መሰል የሰብዓዊነት ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። ህፃን ብሌን ወደ ውጭ ሀገር ሄዳ ታክማ፣ እንደ እኩዮቿ ቆማ የምታመሰግንበት ቀን ቅርብ እንደሆነም ተገልጿል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ