AMN-የካቲት 27/2018 ዓ.ም
ምርጫ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ ያለዉ ድርሻ የላቀ ነዉ፡፡
ምርጫ ድምጽ የሚሰጥበት ዴሞክራዊያዊ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን፣ የሕዝብ ሉዓላዊነት የሚረጋገጥበትና የመንግሥት ሥልጣን ሕጋዊነት የሚያገኝበት መሠረታዊ ሂደት ነው።
ምርጫ የሥልጣን ምንጭነትን ከማረጋገጥ፣ ተጠያቂነትን ከማስፈን፣ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርን ከማረጋገጥ፣ የህዝብ ተሳትፎን ከማሳደግና የፖለቲካ ብዝሃነትን ከማበረታታት ረገድ የሚኖረዉ ሚናም የላቀ ነዉ፡፡
በዴሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት ነው። ምርጫ ደግሞ ሕዝቡ በራሱ ፈቃድና ምርጫ የሚመሩትን ሰዎች እንዲሰይም ዕድል የሚያገኝበት ነዉ፡፡
ይህ ሂደት “የመንግሥት ሥልጣን የሚመነጨው ከሕዝብ ነው” የሚለውን መርህ በተግባር ለመተርጎም ይረዳል።
ዴሞክራሲ የጥቂቶች ጉዳይ ባለመሆኑ ምርጫ ዜጎች በአገራቸው የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ በቀጥታ እንዲሳተፉ፣ አማራጭ የፖሊሲ ሃሳቦችን እንዲመዝኑና የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን እንዲወስኑ ያነቃቃል።
የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሃሳብ ብቻ እንዲወዳደሩ ምቹ መዳላደልን ይፈጥራል፡፡ ይህም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ድምጻቸዉን እንዲያሰሙ እና በፓርላማ ውስጥ ወኪል እንዲያገኙ ዕድል ይፈጥራል።
በኢትዮጵያ የሚካሄደዉ 7ኛዉ ጠቅላላ ምርጫም መራጩ ሕዝብ በራሱ ፈቃድና ምርጫ የሚመሩትን ሰዎች እንዲሰይም ዕድል የሚያገኝበት ከመሆኑም በላይ ዜጎች በአገራቸው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ በቀጥታ እንዲሳተፉ፣ አማራጭ የፖሊሲ ሃሳቦችን እንዲመዝኑና የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን እንዲወስኑ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ7ኛዉ ጠቅላላ ምርጫ ባወጣዉ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የመራጮች ምዝገባ መጪዉ ቅዳሜ የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ይጀመራል፡፡
የመራጮች ምዝገባዉ በቦርዱ አዲስ መተግበሪያ አልያም በአካል በሚደረጉ የዲጂታል ምዝገባዎች እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታዉቋል፡፡
በአጠቃላይ ካሉት 45 ሺህ ምርጫ ጣቢያዎች መካከል በ17 ሺህ ጣቢያዎች ላይ የዲጂታል ምዝገባ ሥርዓቱ ተግባራዊ እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ