AMN- የካቲት 26 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በማስመልከት የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጮቻቸውን የሚያቀርቡበትን “የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ” የክርክር መድረክ አካሄደ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የሚንቀሳቀሱ 17 የፖለቲካ ድርጅቶች በፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አማካኝነት በሚዲያ አጠቃቀምና በምርጫ ሥነ-ምግባር ላይ ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር በመተባበር ስልጠና መውሰዳቸው ይታወሳል፡፡
ፓርቲዎቹ በክርክሩ እንዲሳተፉ አራት አራት ሆነው የተደለደሉ ሲሆን፣ በዛሬው የመጀመሪያ ዙር ክርክር ብልጽግና ፓርቲ፣ ህብር ኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያ ህዳሴ ፓርቲ ተሳትፈዋል፡፡

ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ እንደማይሳተፍ በመግለጹ ክርክሩ በሦስቱ ፓርቲዎች መካከል ተካሂዷል፡፡
ተፎካካሪ ፓርቲዎች አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ውድ የሆነውን የአየር ሰዓት ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በነፃ ማመቻቸቱን አድንቀዋል፡፡
በተለይም ከክርክሩ በፊት ስለ ሚዲያ አጠቃቀምና ሥነ-ምግባር ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መዘጋጀቱ ልዩና የሚያስደንቅ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ፓርቲዎቹ በክርክር መድረኩ “መራጩ ሕዝብ ይግዛን፣ ሀገርን ያሻግራል” ያሏቸውን የፖሊሲ አማራጮች በልዩ ስሜት ለሕዝብ አቅርበዋል፡፡

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ ምርጫው ፍትሐዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ተቋሙ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንደሚወጣ ገልጸዋል፡፡
የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱ እንዲጎለብት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ድምፃቸውን በነፃነት የሚያሰሙበትን ዕድል ተቋሙ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
የተቋሙ የምርጫ ዴስክ በቀጣይም በአዲስ አበባ ከተማ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ከአራት ክፍሎች በላይ የሆኑ የክርክር መድረኮችን ለማካሄድ ግብ አስቀምጦ እየሠራ እንደሚገኝ ተመልክቷል፡፡
በአልዓዛር መኮንን