AMN የካቲት 26/2018
የ1447ኛው የረመዳን ፆም ወርን ምክንያት በማድረግ የሚዘጋጀው የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርሀ ግብር የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም በመላ ሀገሪቱ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ።
ለስድስተኛ ጊዜ የሚካሄደው ሀገር አቀፍ የኢፍጣር መርሀ ግብርን የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጋር በመተባበር መዘጋጀቱ ተገልጿል።
ምክር ቤቱ መርሀ ግብሩን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ የዘንድሮው የኢፍጣር መርሃግብር “ነጃሺ ለሀገር” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እና በተመረጡ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በተመሳሳይ ቀን የሚከናወን ይሆናል።
የጠቅላይ ምክር ቤቱ የፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት ኃላፊ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ በመግለጫው ወቅት፤ የፊታችን ቅዳሜ የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም በመላ ሀገሪቱ የአደባባይ ኢፍጣር መርሃ-ግብር እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
መርሀ ግብሩ የመተሳሰብ እና የመረዳዳት እሴቶችን የሚያጎለብት መሆኑን ገልጸው፤ በተጨማሪም ለሀገሪቱ የከፍታ ጉዞ የሚጠበቅብንን አስተዋጽኦ ለማበርከት ቃላችንን የምናድስበት ነው ብለዋል።
የኢፍጣር መርሃግብሩን ለማከናወን ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸው፤ ህዝበ ሙስሊሙ ወደ ኢፍጣሩ ስፍራ ሲሄድ በእስልምና አስተምህሮት መሰረት ሊሆን ይገባል ሲሉም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል ፕሬዝዳንት ኡስታዝ ሀይደር ከድር በበኩላቸው እንደገለጹት፣ የዘንድሮው ኢፍጣር በዓይነቱ ለየት ያለና በአንድ ቀን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚካሄድ ነው።
ይህም ወጣቶች ለአንድነት፣ ለልማትና ለእድገት ያላቸውን ሚና የሚያጠናክሩበት መርሃ ግብር ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የልማትና ማሕበራዊ ዘርፍ ምክትል ፕሬዝደንት ሼይኽ ሐሚድ ሙሳ፣ አቅም የሌላቸውን ወገኖች ማገዝ እና መደገፍ በፈጣሪ ዘንድ እጅግ የሚወደድ ተግባር በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
መርሃግብሩ አንድነት እና መተባበር የሚጠናከርበት ከመሆኑ ባሻገር ለሀገር መልካም ገፅታ ግንባታም ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡